የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ ልማት ማፍለቂያ ማዕከል የቢዝነስ ሃሳብ አቅርበው ማጣሪያውን ላለፉ 5 የ2014 ዓ/ም ዕጩ ተመራቂ ተማሪዎች መስከረም 26/2014 ዓ/ም ሽልማት አበረከተ፡፡

የቀረቡት የቢዝነስ ሃሳቦች የምግብ ተረፈ ምርቶችን ወደ ጋዝ ምርት መቀየር፣ የሸክላ ውጤቶችን ማስዋብና ለገበያ ተወዳዳሪ አድርጎ ማቅረብ፣ ፕላስቲክ ጫማዎችን አዘምኖ ለገበያ ማቅረብ፣ ኤሌክትሮኒክ የሕክምና አገልግሎት መስጠትና ኤሌክትሮኒክ የሕግ (ጥብቅና) አገልግሎት መስጠት ናቸው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በማጣሪያ ውድድሩ 1ኛ ተማሪ ኪሩቤል ጌታቸው 66.43 በማምጣት 10 ሺህ ብር፣ 2ኛ ተማሪ ዳዊት ገ/ማርያም 64.43 በማምጣት 7 ሺህ ብር፣ 3ኛ ተማሪ ኪሩቤል መንግሥቱ 57.17 በማምጣት 5 ሺህ ብር፣ 4ኛ ተማሪ መክሊት ወ/ሰንበት 56.93 በማምጣት 3 ሺህ ብር እና 5ኛ ተማሪ ዳዊት ግርማ 54.94 በማምጣት 2 ሺህ ብር የተሸለሙ ሲሆን የዕውቅና የምሥክር ወረቀትም ተበርክቶላቸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዓለም ላይ ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች መነሻቸው የተጠና የዝቅተኛ ቢዝነስ ሃሳብ በመሆኑ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡ ያደጉ ሀገራት የእድገት ምንጭ የዜጎች የሥራ ፈጠራ ክሂሎት ማደግና ክሂሎታቸውን ወደ ተግባር መቀየራቸው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሥራ ማፍለቂያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ እንዲያግዝ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅና በማኔጅመንት ት/ክፍል ሃሳብ አመንጪነት ‹‹የሥራ ፈጠራ ልማት ማፍለቂያ ማዕከል›› መመሥረቱን ገልጸዋል፡፡ ማዕከሉ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ በከተማዋ ለሚገኙ ወጣቶችና ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ሥልጠና መስጠቱ እንዲሁም የቢዝነስ ሃሳብ ውድድር ማካሄዱ ለአብነት የሚጠቀሱ ተግባራት ናቸው ብለዋል፡፡

የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወልደመድኅን በመዝጊያ ንግግራቸው ማዕከሉ ይህንን ዓይነት መድረክ በማዘጋጀት ተማሪውን ስለ ቢዝነስ ሃሳብ ግንዛቤ እንዲጨብጥና የቢዝነስ ሃሳብ አቀራረብን እንዲገነዘብ መደገፉ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው ማዕከሉ ይህንን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ብለዋል፡፡

ተወዳዳሪ ተማሪዎች ባገኙት ሽልማት መደሰታቸውን ገልጸው በተሰጠን አስተያየት መሠረት የተሻለ የቢዝነስ ሃሳብ እናዘጋጃለን ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ሥራ ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ኃላፊ፣ የአ/ምንጭ ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የአ/ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳተላይት ማሠልጠኛ ኮሌጅ ም/ዲን፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ተመራቂ ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ዝግጅቱን ታድመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት