የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል አውስትራሊያ ሀገር ከሚገኘው “Menzies School of Health Research” ከተሰኘ የጤና ምርምር ት/ቤት ጋር ‹‹Effectiveness of Novel Approaches to Radical Cure of Vivax Malaria with Tafenoquine and Primaquine›› በሚል ርዕስ 210 ሺህ ዶላር የተመደበለት ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት ለማከናወን ጥቅምት 5/2014 ዓ/ም የመግባቢያ ስምምነት በቨርችዋል ተፈራርመዋል፡፡  

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተርና የምርምር ፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ እንደገለጹት የምርምር ሥራው በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በሚገኘው ‹‹Clinical Trail›› ማዕከል ውስጥ የሚደረግ ነው፡፡ የምርምር ፕሮጀክቱ በዋናነት ቫይቫክስ ተብሎ ለሚጠራው የወባ በሽታ ዓይነት የሚሰጡ ‹‹Tafenoquine›› እና “Primaquine›› የተሰኙ መድኃኒቶችን ውጤታማነትና ፈዋሽነትን መፈተሽን ዓላማ በማድረግ ለሁለት ዓመታት የሚደረግ ጥናት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም መሰል የምርምር ሥራዎች በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ መሪነት ሲካሄዱ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ታምሩ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መሰል ምርምሮችን ለማካሄድ የሚያስችል የሰው ኃይል፣ የምርምር ፕሮቶኮሎችን የማዘጋጀትና ሌሎች አቅሞች መፍጠር በመቻሉ ምርምሩን በሙሉ ኃለፊት መውሰድ ችሏል ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ዶ/ር ታምሩ እንደተናገሩት ቫይቫክስ የተሰኘው የወባ በሽታ ዓይነት ሰውነት ውስጥ ተደብቆ በመቆየት ምቹ ሁኔታ ሲያገኝ በተደጋጋሚ የመከሰት ባህሪ አለው፡፡ የምርምር ፕሮጀክቱ ዋነኛ ትኩረትም ለበሽታው በሦስት ዓይነት መንገድ የሚሰጡትን ሁለቱን መድኃኒቶች ለታማሚዎች በመስጠትና ለ6 ወራት ክትትል በማድረግ የትኛው መድኃኒትና ዘዴ ይበልጥ ውጤታማ እንደሆነና ዳግም በሽታው በሰውነት ውስጥ ተደብቆ እንዳይነሳ የማድረግ አቅም እንዳለው የሕክምና ምርምር አሠራር ዘዴንና ሥነ-ምግባርን በተከተለ መንገድ መለየት ነው፡፡

በዓለም ላይ የወባ ስርጭትን በዘላቂነት ለማጥፋት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ታምሩ የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆኑ መሰል ጥናቶች በካምቦዲያና ኢንዶኔዥያ የሚካሄዱ በመሆናቸው የምርምር ሥራዎቹ ውጤቶች ፋይዳቸው አገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በ “Menzies School of Health Research” ዋና ተመራማሪ Dr Kamala Trimer (ዶ/ር ካማላ ትሪመር) በስምምነቱ ወቅት በሰጡት አስተያየት ተቋማቸው በኢትዮጵያ አንጋፋና የምርምር ዩኒቨርሲቲ ከሆነው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሥራቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው የምርምር ፕሮጀክቱም ወባን ከዓለም ላይ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን ሚና የሚጫወት ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ካማላ ተቋማቸው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚደረገው የምርምር ሥራ ውጤታማ እንዲሆንና የታለመለትን ግብ እንዲመታ ለማስቻል በውል ስምምነቱ መሠረት አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋልም ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዓለም አቀፋዊ የትብብር ሥራዎችን መሥራት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ

መሰል በትብብር የሚሠሩ ግዙፍ የምርምር ፕሮጀክቶችን በማግኘት ምርምር ለማከናወን መግባባት ላይ መደረሱ እንደ ዩኒቨርሲቲ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር ነው ብለዋል፡፡

የምርምር ፕሮጀክቱን ለማከናወን የሚያስችል በቂ የሰው ኃይልና መሠረተ ልማት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በኩል መኖሩ የተገለጸ ሲሆን የሕክምና ምርምር ት/ቤቱም በበኩሉ ለምርምር ሥራው የሚሆነውን በጀት ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ይሆናል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬ