የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት በጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር ጥቅምት 20/2014 ዓ/ም ክላስተራዊ የውይይት ፎረም አካሂዷል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት ዳይሬክቶሬቱ ከሚሠራቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል የተማሪዎችን የንድፈ ሃሳብ ዕውቀት ከቴክኖሎጂና ከኢንደስትሪ ጋር በማስተሳሰር ክሂሎታቸውን ማሳደግ አንዱ ሲሆን ለአካባቢው ማኅበረሰብ ችግር ፈቺ እና ጊዜና ጉልበት ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን የማሸጋገር ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ለዚህም ከተለያዩ የፌዴራልና የክልል ተቋማት ጋር በምርምር፣ የመምህራንን አቅም በማጎልበትና በኤክስተርንሺፕ የትምህርት ዕድል በመስጠት በጋራ እንደሚሠራ ዶ/ር ቶሌራ ተናግረዋል፡፡ ክላስተራዊ ፎረሙ በአካባቢው የሚገኙ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ የቴክኒክና ሙያ እና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎችን በመደገፍ፣ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ የዕውቀት ሽግግር በማድረግና በጋራ በመሥራት ክሂሎታቸውን ለማሳደግ እንዲሁም የሥራ ፈጠራና የገበያ ትስስርን ለመፍጠር የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ፖሊ ሳታላይት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክተርና የፎረሙ ጸሐፊ አቶ ወርቅነህ ኃ/ሚካኤል ፎረሙ ጥቅምት/2010 ዓ/ም መመሥረቱን ገልጸው ዓላማው በዋናነት የዕውቀት ሽግግር ማድረግ፣ የኢንደስትሪውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ ቴክኖሎጂን መቅዳትና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲሁም በሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ አብሮ መሥራትና ጥናትና ምርምር ማካሄድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ፎረሙ ለ7 መምህራን የ2ኛ ዲግሪ፣ ለአንድ መምህር ከፍተኛ ዲፕሎማና ለ20 የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ዕድል መስጠቱን የገለጹት አቶ ወርቅነህ በዩኒ/ኢን/ትስ ፎረም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በኩልም የዳሰሳ ጥናት ተካሂዶ ችግሮች መለየታቸውንና ለመፍትሄው የጋራ ግንዛቤ ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

የኮንሶ-ካራት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ም/ዲን አቶ መሠለ ይመር ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የሚቀጠሩ ባለሙያዎች ላይ የተግባር ዕውቀት ክፍተት እንዲሁም በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተማሪዎች ላይ የንድፈ-ሃሣብ ዕውቀት ክፍተት እንደሚታይባቸው ተናግረዋል፡፡ የጋራ ፎረሙ ይህን መሰል ችግሮችን ለመቅረፍና ክፍተቶችን ለመሙላት ይረዳል ብለዋል፡፡

በመድረኩ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዋና ዋና ተግባራት፣ የፎረሙ አመሠራረትና በጋራ የተሠሩ ሥራዎች፣ የ2014 ዓ/ም የጋራ ዕቀድ፣ በዩኒ/ኢን/ትስ ፎረም የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ዳሰሳ ጥናት፣ በአጫጭር ሥልጠና እና ጥናትና ምርምር የባለድርሻ አካላት ሚና ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡

 

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት