የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህሪ ሳይንስ ት/ቤት ‹‹የትምህርት ምዘናና ግምገማ ሚና ለትምህርት ጥራት›› በሚል ርዕስ ለትምህርት አመራር አካላት ኅዳር 1/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምዘናና ግምገማ አስፈላጊነት፣ የምዘናና ግምገማ አጠቃላይ መርሆዎች፣ የፈተና አደረጃጃት፣ የፈተና እርማት እና ከምዘናና ግምገማ ሥራ አንጻር የሚስተዋሉ ክፍተቶች ከሥልጠናው ይዘቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ምዘናና ግምገማ በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ መምህራን ከሚተገብሯቸው ተግባራት መካከል ቁልፉ ቢሆንም ሥራው በአብዛኛው የሀገሪቱ የትምህርት ተቋማት ላይ ክፍተት ይታይበታል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ችግሩን ለመቅረፍ ለነባር መምህራን በከፍተኛ ዲፕሎማ ደረጃ ሥልጠና የሚሰጥ ሲሆን አዲስ ተቀጣሪ መምህራንን ለ36 ሰዓት ስለ ሥነ-ትምህርት ያሠለጥናል ብለዋል፡፡ አመራር አካላት በግምገማና ምዘና ዙሪያ ክፍተቶች ሲፈጠሩ የሚቆጣጠሩበትና አስተያየት የሚሰጡበትን ክሂሎት እንዲያሳድጉ የአመራር አካላት ሥልጠናው መዘጋጀቱን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ አመራር አካላቱ ሥልጠናውን መውሰዳቸው ለተማሪው የጊዜ ብክነትን የሚቀንስ፣ ተገቢ ትምህርት እንዲያገኙ የሚያደርግና በፈተና ወቅትም ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መምህራን ለሥራቸው ትኩረት ሰጥተው ተማሪዎችን በተገቢው መንገድ እንዲመዝኑና እንዲገመግሙ፣ ፈተናዎችን አስቀድመው እንዲያዘጋጁ እንዲሁም የኮርሱ ዓላማና ፈተናው እንዲገናኝ የሚያደርግ በመሆኑ በቀጣይ ኮሌጆችና ት/ክፍሎች ሥልጠናውን ወደ መምህራን ማውረድ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የሥነ-ትምህርት ት/ክፍል መምህርና የሥልጠናው አስተባባሪ ዶ/ር ግርማ መኩሪያ ሥልጠናው የምዘናና ግምገማ አተገባበርን ወጥና ዘመናዊ በማድረግ ከትምህርት ጥራት ጋር ለማስተሳሰር የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሥነ-ትምህርት ት/ክፍል ኃላፊና ሠልጣኝ አቶ ሰለሞን ሳጶ በተከታታይ ምዘናና ግምገማ ወቅት ፈተናና አሳይመንት ሰጥቶ ማርክ ከመመዝገብ ባለፈ ተማሪው ኮርሱን በሚገባ መከታተሉንና ፈተናዎች ከኮርሱ ዓላማ ጋር መገናኘታቸውን ጭምር የምንከታተልበት መሆኑን ከሥልጠናው ተረድቻለሁ ብለዋል፡፡

በሥልጠናው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት፣ ም/ፕሬዝደንቶችና የሁሉም ካምፓሶች የትምህርት አመራር አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት