የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ለባለድርሻ አካላት፣ ለቢሮ ኃላፊዎችና ከ19ኙ ቀበሌያት ለተወጣጡ 70 በጎ መልዕክተኞች ከኅዳር 2-4/2014 ዓ/ም በአስተሳሰብ ለውጥና በማኅበራዊ ጉዳይ ተግባራት ላይ የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ እንደገለጹት ሠልጣኞች እስከ አሁን የመጡበትን መንገድ እንዲፈትሹ፣ የተሳሳቱትን እንዲያርሙና ወደ ፊት የሚጓዙበትን የሕይወት መንገድ እንዲያዩ የአመለካከት ለውጥን ለማምጣት የሚያግዝ ሥልጠና ነው፡፡

ሥልጠናው በአረጋዊያን፣ በወላጅ አጥ ሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞች፣ በጎዳና ተዳዳሪዎችና አቅመ ደካማ በሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ በአመለካከት መዛባት ምክንያት የሚደርስባቸውን ማግለልና መድልኦ በማስቀረት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚረዳ መሆኑን የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ውቢት ተፈሪ ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ጽ/ቤት የሰው ሀብት ቡድን መሪና የሥልጠናው ተሳታፊ ወ/ሮ እማዋይሽ ምናለ ከሥልጠናው ባገኙት ክሂሎት ራሳቸውንና ሌሎችን ለመለወጥ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የቆላ ሻራ ቀበሌ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ተወካይና የቀበሌው የበጎ አድራጎት ማኅበር ም/ሰብሳቢ አቶ ጌትነት ላይና በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች በአመለካከት ችግሮች የሚቀሰቀሱ መሆናቸውን ጠቅሰው የአመለካከት ለውጡን ከራሴና ከቤተሰቤ ለመጀመር ወስኛለሁ ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት