አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት 10 ሚሊየን ብር እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች የሚውል አንድ ሚሊየን ብር የሚያወጣ የምግብ እህል ድጋፍ ኅዳር 14/2014 ዓ/ም አድርጓል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ በማስተባበር የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እንዲሁም የደም ልገሳ ድጋፎችን ለመከላከያ ሠራዊትና በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የወር ደምወዛቸውን ለሠራዊቱ ለመስጠት ቃል መግባታቸውን የተናገሩት ዶ/ር ዳምጠው የዛሬውን ጨምሮ 13 ሚሊየን ብር ለሠራዊቱ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በቀጣይም 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ከቁሳቁስና ገንዘብ ድጋፉ ባሻገር ከ100 በላይ የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ወደ ግንባር ዘምተው በዘመቻው ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች የምግብ እህልና የአልባሳት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው በዛሬው ዕለትም በደብረ ብርሃን ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚውል 170 ኩንታል የጤፍ ዱቁት እና 30 ኩንታል የአተር ሽሮ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ የተጀመረው የሕልውና ዘመቻ እስኪጠናቀቅ ጊዜ ድረስ ዩኒቨርሲቲው ለመከላከያ ሠራዊቱም ሆነ ለተፈናቃይ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲውና መላው ማኅበረሰብ ለሀገር ሕልውና ቅድሚያ በመስጠት እያሳዩ ያለው ደጀንነት የሚደነቅ ነው፡፡ ሚኒስትር ዴኤታዋ የሕልውና ዘመቻው ተጠናቆ የሀገራችን ሰላምና ሉዓላዊነት እስኪረጋገጥ ድረስ በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከመደበኛ ሥራቸው ባሻገር በተለያየ ሁኔታ እንቅስቃሴ በማድረግ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መሆናቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የተደረገውን የምግብ እህል ድጋፍ የተረከቡት የኢፌዴሪ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ለሁለተኛ ጊዜ ድጋፍ ማድረጉ ዩኒቨርሲቲው የተጣለበትን ማኅበራዊ ኃላፊነት እየተወጣ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍ በተፈናቃዮቹ ስም ምስጋናቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ኤርጎጌ መሰል ተቋማትም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ፈለግ በመከተል የተጀመረው የሕልውና ዘመቻ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት