‹‹አሜሪካና ምዕራባውያን ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ላይ ያላቸው ፍላጎት›› በሚል ርዕስ ኅዳር 25/2014 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውይይት ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ኃ/ሚካኤል ዴቢሳ ባለንበት ዘመን የዲፕሎማሲ ሥራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማቋቋም፣ በየሀገሩ አምባሳደር በመሾምና ዲፕሎማቶችን በመቅጠር ብቻ የሚከናወን አለመሆኑን ተናግረው ሁሉም ዜጎች የተለያዩ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም በዕውቀት የሚሟገቱ ዲፕሎማቶች ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ተማሪዎችም እንደ ‹‹Twitter›› እና ‹‹Facebook›› ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም በሚደረጉ ዘመቻዎች ላይ የሀገራቸው ጠበቃና ተሟጋች በመሆን የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት በመሆኗ ኢትዮጵያን መምታት አፍሪካን መምታትና ማንበርከክ ተደርጎ የሚታሰብ በመሆኑ ሀገራችን ላይ የሕወሓት አሸባሪ ቡድንን በመጠቀም የተከፈተብን ጦርነት መላው አፍሪካንና ጥቁር ሕዝቦችን ማንበርከክን ዓለማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር፣ ተመራማሪና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሀገረ መንግሥት ያላት ሀገር እንደሆነችና በተለያዩ ጊዜያት ፈተናዎች የገጠሟት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አብዛኞቹ ፈተናዎች የዓባይ ወንዝን ለመቆጣጠር ከሚደረጉ ጫናዎች የመነጩ ናቸው ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ ኢትዮጵያ በታሪኳ ጫናዎችና ፈተናዎችን ተቋቁማ በአሸናፊነት መቀጠሏን አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣው ጦርነት አዲስ ባለመሆኑ ይህንን ፈታኝ ጊዜ ለመሻገር እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዜጎች መትጋት በተለይ የተማረው ማኅበረሰብ ዕውቀቱን ሀገርን ለማዳን መጠቀም ይኖርበታል ብለዋል። ጦርነት ውስጥ የገባነው ከአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ጋር ብቻ አለመሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ያዕቆብ እየተዋጋን ያለነው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ከሆኑና በኢትዮጵያ ተላላኪ መንግሥት እንዲኖር ከሚፈልጉ እንደ አሜሪካና ምዕራባውያን ሀገራት ጋር ጭምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ኃያላን ሀገራት እንደ ሕወሓት ያሉ አሸባሪ ድርጅቶችን በመጠቀም ኢትዮጵያ የምትባል ጠንካራ መንግሥት ያላት ሀገር እንዳትኖር እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአሸናፊነት እንጂ የተሸናፊነት ታሪክ የላትም ያሉት ዶ/ር ዳምጠው ይህንን በሀገራችን ላይ የተከፈተውን ጫናና ሴራ ለመቋቋም እንደ ሀገር ጠንካራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከላት በዩኒቨርሲቲዎች መቋቋማቸው በተቋማቱ የሚገኙ ምሁራንና ተማሪዎችን በማሳተፍ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ በአርባ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው ማዕከልም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት በዕውቀትና በእውነት ላይ ተመሥርተው ሀገራቸውን እንዲያስተዋውቁና ሀገራቸውን በዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘርፍ እንዲያግዙ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል ብለዋል፡፡

በዕለቱ ከቀረቡ የመወያያ ጽሑፎች መካከል ‹‹የዓባይ ወንዝን የሚጋሩ ሀገራት ግንኙነት፣ ፍላጎትና የጥቅም ግጭት ታሪካዊ ዳራ›› በሚል ርዕስ በመ/ር ያምራል መኮንን የቀረበው የሚጠቀስ ሲሆን የጽሑፉ አቅራቢ የዓባይ ወንዝ ከጥንት ጀምሮ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ማዕከል መሆኑንና ወንዙን በሚጋሩ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት፣ ፍላጎትና የጥቅም ግጭት ተለዋዋጭና ያልተረጋጋ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተለይ ግብጾች የዓባይ ወንዝን ለመቆጣጠር በኢትዮጵያ ላይ የፊት ለፊት ጦርነት ከማድረግ ጀምሮ በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ አማጺና ተገንጣይ ኃይሎችን በመደገፍ ጭምር ይሠራሉ ያሉት መ/ር ያምራል ለወንዙ 86 ከመቶ በላይ የምታበረክተውን ኢትዮጵያን ያላሳተፉ የቀኝ ግዛት ስምምነቶችን በመጥቀስ ጭምር ሀገሪቱ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማሳደር በስፋት ይሠራሉ ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ዓለማየሁ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘርፍ ከመደበኛው የዲፕሎማሲ ሥራ ጋር በመቀናጀት እየተሠራ ያለበት በመሆኑ ዜጎች የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም ለሀገራቸው ዲፕሎማት መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ በሀገር ጉዳይ እያንዳንዱ ዜጋ ከዳር ቆሞ ማየት የለበትም ያሉት አቶ ተስፋዬ ሁሉም ዜጋ ‹‹እኔም የሀገሬ ዲፕሎማት ነኝ›› በሚል መርህ ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም በዕውቀትና እውነት ላይ ተመሥርቶ የሚሟገት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ከውይይት መርሃ-ግብሩ አስቀድሞ የዩኒቨርሲቲው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በዲጂታል ዲፕሎማሲና በ‹‹የዓባይ ልጆች›› ሶፍትዌር አጠቃቀም ዙሪያ ኅዳር 24/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት