የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህሪ ሳይንስ ት/ቤት የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከአርባ ምንጭ ከተማ 4 የግል ት/ቤቶች ለተወጣጡ መምህራን የግምገማ አሰጣጥና የምዘና ሂደት፣ ስሜትን የመረዳትና የማንበብ ብቃት፣ ሙያዊ ፍቅር፣ የማስተማሪያ ሥነ-ዘዴና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከኅዳር 17-18/2014 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህሪ ሳይንስ ት/ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋን ማፍራት የትምህርት ዋነኛ ግቡ እንደመሆኑ ይህንን ለማሳካት ከታች ጀምሮ ያለው የትምህርት አሰጣጥ ወሳኝነት ያለው ስለሆነ በየወቅቱ አቅምን የሚያሳድጉ ሥልጠናዎችን በመውሰድና የመረጃ ምንጮችን በመጠቀም ራስን ማንቃትና በዕውቀት ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

የት/ቤቱ የማኅበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪና አሠልጣኝ አቶ ዘበነ ተምትሜ እንደገለጹት መምህራኑ ሥልጠናውን መውሰዳቸው ውስጣዊ ተነሳሽነት የሚፈጥርላቸው፣ የማስተማር ክሂሎታቸውን የሚያሳድግና ለተማሪዎች የተሻለ አቀራረብ እንዲኖራቸው የሚያግዝ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ኮሚኒቲ አጸደ ሕፃናት ት/ቤት ር/መምህርትና ሠልጣኝ ወ/ሪት ሳራ ጎይዳ ሥልጠናው የቅድመ መደበኛ ተማሪን እንዴት መረዳትና መመዘን እንደሚችሉ ግንዛቤ የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወጥ የሆነ የትምህርት ሥራ እንዲኖር ያልተሳተፉ ት/ቤቶችን ተደራሽ በማድረግ ቀጣይነት ያለው ሥራ ቢሠራ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ጉልህ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል፡፡

ሌላው የሥልጠናው ተሳታፊ የደ/ኃ ቅዱስ ገብርኤል የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት መምህር አቶ አሸናፊ ፍሥሐ ለዘወትር የመማር ማስተማር ሥራቸው የሚረዳቸውን ቁምነገር እንዲሁም ለግል ሕይወታቸው የሚረዳቸውን የሥነ-ልቦና ትምህርት መጨበጣቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በሥልጠናው ከቅድመ መደበኛና 1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተወጣጡ 145 ሠልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት