የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ በ ‹‹ArcGIS and Remote Sensing›› ሶፍትዌር አጠቃቀም ዙሪያ 2ኛና 3ኛ ዲግሪ ላላቸው መምህራን እንዲሁም የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች ኅዳር 23/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሌጁ ም/ዲንና የሥልጠናው አስተባባሪ አቶ ኤርሚያስ በፈቃዱ እንደገለጹት ሶፍትዌሩ ለአካደሚክ ዘርፍ ባለሙያዎችና ለድኅረ ምረቃ ተማሪዎች መሰጠቱ ፈጣን የመረጃ ልውውጥን በማስቻል ውጤታማ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲከናወን ስለሚያግዝ ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡ የ''ArcGis'' ሶፍትዌር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ''Environmental Systems & Research Institute/ESRI'' ጋር ባደረገው የትብብር ግንኙነት አማካኝነት የተገኘ ሲሆን ሶፍትዌሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በውድ ዋጋ ከሚሸጡ ሶፍትዌሮች አንዱ መሆኑን አቶ ኤርሚያስ ጠቁመዋል።

በማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የጂኦግራፊ ት/ክፍል መምህርና አሠልጣኝ አቶ ደምበል ቦንታ በበኩላቸው እንደተናገሩት በሀገራችን መሰል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ስርዓት መዘርጋቱ ለመማር ማስተማርም ሆነ ለምርምር ሥራ ያለው አስተዋፅዖ ጉልህ ነው። የተገኘው ሶፍትዌርም ያልተገደበ ፈቃድ /unlimited license/ ያለው በመሆኑ ተቋማችን የ''ArcGis Platform'' ለረዥም ጊዜ አቅዶ እንዲጠቀም ያስችላል ብለዋል።

መ/ር ደምበል እንደገለፁት ሥልጠናው ''Desktop GIS /ArcGIS Pro and ArcMap/፣ ''Web GIS /ArcGIS Online'' እና ''Mobile GIS/Feild Apps'' ያካተተ ነው። ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲው ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት እንዲኖር ለሚመለከታቸው አካላት በቀጣይነት የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአንዳንድ ተቋማት በሚፈለገው መልኩ የመረጃ ልውውጥ ያለመኖርና መረጃዎችን ከኢንተርኔት ለማውረድ ብዙ ሰዓት የሚፈጅ መሆኑን የጠቀሱት አሠልጣኙ ሶፍትዌሩ 95 በመቶ በሚሆን ደረጃ ከጂኦቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ቀላልና ምቹ እንዲሁም ፈጣን የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት