16ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ‹‹ወንድማማችነት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት›› በሚል መሪ ቃል ኅዳር 29/2014 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በራሳቸውና በሀገራቸው ላይ የሚቃጣባቸውን የውስጥና የውጭ የህልውና አደጋ ለመከላከል ኅብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን ማጠናከርና ለጋራ ዓላማ አብሮ መቆም ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት ሀገሪቱ የገጠማት ጦርነት በቶሎ እንዲጠናቀቅ እንዲሁም የተፈናቀሉ ወገኖችንና የተጎዱ የማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በማቋቋም ዙሪያ እየተደረገ ያለው ድጋፍና ትብብር የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ አሁን ካለው ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን የምናከብረው ኢትዮጵያዊነት እንደ አለት በጠነከረበትና በተሳሳተ ትርክት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን ኃይል በተባበረ ክንድ ድል እያደረግን ባለንበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በድሩ ሂሪጎ ዕለቱን በተመለከተ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሠነድ የጋራ ታሪኮች፣ አመለካከቶች፣ ባህሎችና የጋራ ስነልቦና ውቅር በአንድ ሀገር ውስጥ ባሉ ሕዝቦች መካከል ወንድማማችነት ስለ መኖሩ መገለጫዎች መሆናቸውን ጠቅሰው በብሔሮችና ብሔረሰቦች መካከል አያያዥ ክሮች መኖራቸው ለጋራ ስኬት እንዲተጉና እንዲተባበሩ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሰላም ፎረም ፕሬዝደንት ተማሪ ጴጥሮስ ሀሮ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የገጠመን ችግር በኅብረ ብሔራዊ ዘመቻ እየተደመሰሰ ባለበት ሁኔታ በዓሉ መከበሩ የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ለየት ያደርገዋል ብሏል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ የተማሪ ተወካዮችና የአስተዳደር ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን በመጨረሻም የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቃወም #NoMore! (በቃ!) የሚሉ መፈክሮች ተደምጠዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት