የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከጋሞ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ጋር በመተባበር ለICT ባለሙያዎች ከኅዳር 20-25/2014 ዓ/ም የ‹‹Advanced Web Development›› ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የጋሞ ዞን አስተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ ሽመልስ ታደሰ በመክፈቻ ንግግራቸው የሀገራችንን ኢኮኖሚ ከግብርና መር ወደ ኢንደስትሪ መር ለማሸጋገር የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ራሱን ችሎና በምርምር ላይ ተመሥርቶ ለውጥ ማምጣት በሚችልበት መልኩ መንቀሳቀስ ስላለበት ከሚኒስቴር ጀምሮ በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ወርዶ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ሠልጣኞች በሚሠሩበት መዋቅር ሁሉ አመራሩንም ጭምር የማሠልጠንና የማብቃት አቅም ለመፍጠር በትኩረት መሠልጠን እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ዩኒቨርሲቲው ከጋሞ ዞን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራት መስማማታቸውንና ሥልጠናውም የስምምነቱ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ሠልጣኞች ባገኙት ክሂሎት ውጤታማ ሥራ እንደሚሠሩ ተስፈኛ ነኝ ብለዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ሙሉጌታ በበኩላቸው ሥልጠናው ዘመናዊ ድረ-ገጽ የማዘጋጀት ክሂሎታቸውን በማሳደግ በተመደቡበት የሥራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮምፕውተርና ሶፍትዌር ምኅንድስና ፋከልቲ ዲንና በቴምፕሌት 24 ዲዛይን ሶፍትዌር ላይ ሥልጠና የሰጡት አቶ አሚን ቱኒ ሶፍትዌሩ በቀላሉ ኢንተርኔት ባለበት ጊዜ ለመቆጠብ በአንድ ኮምፕውተር ጀርባ ኮድ እየሰጡ የሚፈልጉትን ፕሮግራም መምረጥ፣ ፎቶዎችን መምረጥና ከጽሑፍ ጋር ማቀናጀት፣ ጽሑፎችን አርትኦት ማድረግ እንዲሁም በሰርቨር ላይ መልቀቅና ማሳተም የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ የሶፍትዌርና ድረ-ገጽ አስተዳደር ዳይሬክተርና የሥልጠናው ተሳታፊ አቶ ተሰማ ዘለቀ በአስተያየታቸው ሥልጠናው ከዚህ ቀደም ከሚያውቁት በተጨማሪ ቴክኖሎጂዎችን ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ የአካባቢውን ባህል፣ ታሪክ፣ የተፈጥሮ መስህቦችና ለኢንቬስትመንት ሊውሉ የሚችሉ ቦታዎችን በፎቶና በጽሑፍ በማቀናጀት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ማኅበረሰብ የሚያስተዋውቁበትን መንገድ ከሥልጠናው ማግኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በሥልጠናው የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር፣ የኢንስቲትዩቱ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የጋሞ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ፣ የጋሞ ዞን አስተዳደር ልዩ አማካሪ እንዲሁም ከጋሞ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ፣ ከተለያዩ ወረዳዎችና ከክፍለ ከተሞች የተወጣጡ 28 የICT ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ በሥልጠናው መጨረሻም ለሠልጣኞቹ የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት