የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከደቡብ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲና ከጋሞ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ጋር በመተባበር በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ቆላ ሻራ ቀበሌ እንዲሁም በምዕራብ ዓባያ ወረዳ አንኮበርና ኤልባ ቀበሌያት የሚገነቡትን የባዮ ጋዝ ማብለያዎች ታኅሣሥ 22/2014 ዓ/ም የመስክ ምልከታ አካሂደዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የደቡብ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ወ/ሮ አፀደ አይዛ ኤጀንሲው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ከጋሞ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት መምሪያ ጋር በጋሞ ዞን አምስት ወረዳዎች 1,250 የአርሶ አደር ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ውል ተፈራርሞ ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ የመስክ ምልከታው በመጀመሪያ ዙር በጅምር ላይ ያሉና ተጠናቀው ወደ ሥራ የገቡትን ፕሮጀክቶች በመጎብኘት ሙያዊና ቴክኒካዊ ግብዓቶችን በመውሰድ ለቀጣይ ሥራ ለመነሳሳት ያለመ ነውም ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት በመስክ ምልከታው የታዩት በጅምር ያሉና ሥራቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ የገቡ ፕሮጀክቶች የሚበረታቱ መሆኑን ተናግረው ቀሪ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የሚሸጋገሩ ይሆናል ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ቴክኖሎጂውን በአግባቡ እስኪለማመድና ጠቀሜታውን እስኪረዳ ድረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ከመስጠት ባለፈ የተገነቡ ቴክኖሎጂዎች ረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ከጥገና ጋር ተያይዞ ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንደሚያደርግ ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከደቡብ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በባዮ ጋዝ ማብለያ ቴክኖሎጂ ግንባታ ላይ በጋራ ለመሥራት ከመፈራረሙ አስቀድሞ በዩኒቨርሲቲው እንደ አንድ ግራንድ ፕሮጀክት ተይዞ 1.5 ሚሊየን ብር በላይ በመመደብ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ከዚህ ቀደም ከኤጀንሲው ጋር በጋራ ከሠሯቸው ሥራዎች አንዱ የማዕድን አለኝታ ጥናት ማካሄድ መሆኑን ያስታወሱት ም/ፕሬዝደንቱ በዚህም ወጣቶች በማኅበር ተደራጅተው ማዕድን በማውጣትና በመሸጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ያሉት ተ/ፕ በኃይሉ ባዮ ጋዝን ለምግብ መሥሪያና ለቤት ውስጥ መብራት አገልግሎት ማዋል የደን መመናመንን እና የእናቶችንና የእህቶችን የጊዜና የጉልበት ብክነትን የሚቀንስ፣ በጢስ ከመታፈንና ከጢስ ጋር ተያይዞ ከሚመጣ የመተንፈሻ አካላት በሽታ የሚከላከል እንዲሁም ተረፈ ምርቱ ለማዳበሪያነት የሚጠቅም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው በባዮ ጋዝ ፕሮጀክቱ ዩኒቨርሲቲው ለግንባታ የሚውሉ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ እና ሙያዊና ቴክኒካዊ ድጋፎችን በማድረግ ድርሻውን ይወጣል ብለዋል፡፡ በማገዶ እንጨት ሰበራና በከሰል ማውጣት ሂደት የሚጨፈጨፈውን ደን መጠን በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲስተካካል ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የቆላ ሻራ ቀበሌ ነዋሪ ወ/ሮ አስናቀች መዲና የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ከሆኑ 3 ዓመታትን ማስቆጠራቸውን ተናግረው ለምግብ ማብሰያነት የማገዶ እንጨት ሰበራ ከመሄድና ከመግዛት፣ የምግብ ማብሰያ ዕቃዎች በጢስ ከመበላሸትና የመጸዳጃ ቤት ጉድጓድ በየጊዜው ከማስቆፈር እንደታደጋቸውና የቤት ውስጥ ሥራዎችን በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን እንደረዳቸው ገልጸዋል፡፡ ባዮ ጋዝ የግንባታ ወጪው ቀላል በመሆኑም ሌሎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመስክ ምልከታው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛና የደቡብ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ወ/ሮ አፀደ አይዛን ጨምሮ የጋሞ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች እንዲሁም ከክልልና ከዞን የመጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ ከመስክ ምልከታው መልስ በተደረገው ውይይት ሙያዊና ቴክኒካዊ ሃሳቦች ተነስተው ቀጣይ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት