በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ት/ክፍል ላላፉት 5 ዓመታት የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩት እጩ ዶ/ር ማንጉዳይ መርጮ የካቲት 5/2014 ዓ/ም የውስጥና የውጪ ገምጋሚዎች በተገኙበት የምርምር ሥራቸውን አቅርበዋል፡፡

የመመረቂያ ጽሑፋቸው ‹‹English as a Foreign Language Trainee Teachers’ Perceptions and Reflections on the School-Based Teaching Practice: Three Selected Colleges in SNNP in Focus›› በሚል ርዕስ የተከናወነ ሲሆን አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ በመገኘቱ በአማካሪ ቦርዱ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

እጩ ዶ/ር ማንጉዳይ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በማግኘት በተለያዩ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርነትና በት/ክፍል ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተው ግንቦት 2009 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል አግኝተዋል፡፡

እጩ ዶ/ር ማንጉዳይ በማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ 3ኛው እንዲሁም በእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ት/ክፍል 2ኛው የ3ኛ ዲግሪ ምሩቅ መሆናቸውን የገለጹት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ትምህርት ለአንድ ሀገርም ሆነ ለግለሰብ እድገት መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ባለፈው ዕውቀት ላይ በመመሥረትና የራሳችንን በመጨመር ለመጪው ትውልድ የዕውቀት ሽግግርን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡ ዕውቀት የእድገት ኃይል የሚሆነው ገንቢና አዎንታዊ በሆነ መልኩ ስንጠቀምበት ነው ያሉት ዶ/ር ዓለማየሁ የፍልስፍና ዶክትሬትም በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር የሚገኝ የዕውቀት እድገትና ሽግግር እንዲኖር በማድረግ ረገድ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የድኅረ-ምረቃ ት/ቤት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አበራ ኡንቻ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከ2013 ዓ/ም ጀምሮ በ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ማስመረቅ መጀመሩን አስታውሰው ይህም እንደ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲነቱ የድኅረ-ምረቃ ትምህርት መስክን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነውም ብለዋል፡፡ ፕሮግራሞችን ከማስፋፋት አንፃር 25 የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች የተከፈቱ ሲሆን በ2015 ዓ/ም የሚከፈቱ 3 የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ሥርዓተ ትምህርት እየተዘጋጀ መሆኑንና የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ቁጥርም 293 መድረሱን ዶ/ር አበራ ጠቁመዋል፡፡

በግምገማው መርሃ-ግብር የውስጥና የውጪ ፈታኞችን ጨምሮ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ ዲኖች፣ የት/ክፍል ኃላፊዎች፣ የዘርፉ መምህራንና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት