በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ መንግሥት ፍትሕ ቢሮና በክልሉ በሚገኙ 7 ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በጋራ በተከናወኑ የፍትሕና የሕግ አገልግሎት ሥራዎች አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የላቀ አፈጻጸም በማስመዝገብ የእውቅናና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለቀጣይ 3 ዓመታት የ7ቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ፀሐፊ ሆኖ እንዲሠራም ተመርጧል፡፡ 

የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ከ2012 - 2014 የበጀት ዓመት ከጂንካ፣ ዲላ፣ ወልቂጤ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ዋቸሞ፣ ወራቤና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ያከናወኗቸውን የተለያዩ የሕግ አገልግሎት ሥራዎች የአፈጻጸም ግምገማ የካቲት 05/2014 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ያካሄደ ሲሆን በግምገማው ዩኒቨርሲቲዎቹ በተቋማቸው ያከናወኗቸው የተለያዩ የሕግ አገልግሎት ሥራዎች ቀርበዋል፡፡

ነፃ የሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መቋቋም፣ ከ2012 – 2014 የበጀት ዓመት አጋማሽ በየማዕከላቱ የተሰጡ ነፃ የሕግ አገልግሎቶች፣ የሕግ ንቃተ ኅሊና የሬዲዮ ፕሮግራም፣ በፍርድ ቤት ክርክር የተደረገላቸው ተጠቃሚዎች መጠን እንዲሁም በየማዕከላቱ የተሰጡ ጠቅላላ የሕግ ድጋፎች ብዛትና የተሰጡ ድጋፎች ግምታዊ የገንዘብ ተመን በግምገማው ከተዳሰሱ ነጥቦች መካከል ናቸው፡፡

ነፃ የሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በተመለከተ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ 6 እና በጊዜያዊነት አገልግሎት ያቋረጡ 4 በአጠቃላይ 10፣ በዲላ 6፣ በወላይታ ሶዶ 5፣ በጂንካ 1፣ በዋቸሞ 1 እና በወልቂጤ 1 ማዕከላት መቋቋማቸው ተገልጿል፡፡ ከ2012-2014 የበጀት ዓመት አጋማሽ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ምክር፣ ለሕግ አገልግሎት የሚውሉ ጽሑፎችን በማዘጋጀት እና የጥብቅና አገልግሎቶችን ለ5,818 ወንዶች እና ለ5,045 ሴቶች በድምሩ 10,863 ተገልጋዮች በገንዘብ ሲተመን 40,311,438 ብር በላይ ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በፍ/ቤት የተከራከራቸውን ነፃ የሕግ ድጋፍ ጉዳዮች 98.7 በመቶ የመርታት ምጣኔ ማስመዝገቡ በግምገማው ተነስቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በጠቃላይ በ2 ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የተሠሩ ሥራዎች አበረታችና በተለይም ከአገልግሎት ተደራሽነትና ሰፊ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ እንየው ደረሰ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተቋማዊ በጀትና የተለያዩ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፎችን አግኝተው ቢንቀሳቀሱም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነፃ የሕግ አገልግሎት ሥራ በአንፃሩ የተሻለ እመርታና አፈፃፀም ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ (UNHCR) ጋር ከሚሠራቸው ሥራዎች ልምድ በመቅሰም የተሻለ ነፃ የሕግ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የ2.8 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ ከኤጀንሲው መገኘቱን ዲኑ አስረድተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት