የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከል በአርባ ምንጭ ከተማ ከሚገኙ ት/ቤቶች ለተወጣጡ 100 የ7ኛና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ዓባያ ካምፓስና ዋናው ግቢ በሚገኙ ቤተ-ሙከራዎች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምኅንድስናና ሒሳብ ትምህርት መስኮች ከጥር 28/2014 ዓ/ም ጀምሮ ለ15 ቀናት የሚቆይ የተግባር ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡  

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት STEM ማዕከል በዋናነት ከ7ኛ-12ኛ ክፍል የሚገኙ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን በመለየት በተለይ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና ምኅንድስና ዘርፎች በት/ቤቶቻቸው ማግኘት የማይችሉትን የተግባር ትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ሳይንሱን በተግባር እንዲማሩና እንዲተገብሩ እንዲሁም የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ማስቻልን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በማዕከሉ አማካኝነት ከተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ለተወጣጡ ተማሪዎች መሰል ሥልጠናዎችን በክረምት መርሃ-ግብር ሲሰጥ መቆየቱን ያስታወሱት ዶ/ር ተክሉ አሁን እየተሰጠ ያለው ሥልጠናም በመንፈቀ ዓመት ዕረፍት ላይ የተሰጠ በመሆኑ በዓይነቱ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ከእነዚህ ፕሮግራሞች ባሻገር ከ9ኛ-12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች መሰል ሥልጠናዎችን በሳምንት መጨረሻ ለመስጠት መታቀዱን የጠቆሙት ዶ/ር ተክሉ ይሄው ሥራም የዩኒቨርሲቲው መደበኛ የማኅበረሰብ አገልግሎት ተግባር ሆኖ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው STEM ማዕከል አስተባባሪ ዶ/ር ቢንያም ወንድአለ በበኩላቸው ሥልጠናው በዋናነት ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ተምረው በተግባር ማየት ያልቻሉትን በተግባር እንዲያዩና ትምህርቱ ተጨባጭ እንዲሆንላቸው ለማስቻል የተዘጋጀ ነው፡፡ ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲው በሚገኙ የባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ሒሳብ፣ ኤሌክትሮኒክስና ኮምፕውተር ሳይንስ ቤተ-ሙከራዎች እየተሰጠ መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪው መሰል ሥልጠናዎች በሳይንሱ ዘርፍ እንደ አገር የሚያስፈልጉ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን ከማፍራት አንፃር ፋይዳቸው ጉልህ በመሆኑ ማዕከሉ መሰል ሥልጠናዎችን በተለያዩ መንገዶች መስጠቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ማዕከሉ ከሥልጠናዎች ባሻገር በየአካባቢው ካሉ ት/ቤቶች ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን በማወዳደር ሃሳባቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ የሚያስችል ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በቅርቡ እንደሚጀምርም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

ከሥልጠናው ተሳታፊ ተማሪዎች መካከል ከገሮ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት የመጣችው ተማሪ ሀና ያዕቆብ በት/ቤቷ የተደራጀ ቤተ-ሙከራ ባለመኖሩ በክፍል ውስጥ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የተማሩትን በተግባር የማየት ዕድሉ እንደሌለ ገልጻለች፡፡ በሥልጠናው ከዚህ ቀደም በስዕል ብቻ የምታውቃቸውን እንደ ማይክሮስኮፕ ያሉ መሳሪያዎችን ከማየት አልፋ በተግባር የመጠቀም ዕድል ማግኘቷን የገለጸችው ተማሪዋ ሌሎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የተማረቻቸውን በተግባር ማየት በመቻሏ ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች፡፡ ሥልጠናውን በአግባቡ ለሰጡ የዩኒቨርሲቲው መምህራንም ምስጋናዋን አቅርባለች፡፡

ከሮኆቦት 1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የመጣው ተማሪ በረከት መርዕድ በበኩሉ በዩኒቨርሲቲው ቤተ-ሙከራዎችና መምህራን እየተሰጣቸው ያለው ሥልጠና በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ገልጾ በእስከ አሁን ቆይታቸውም የተለያዩ ሙከራዎችን በመሥራት የተግባር ዕውቀት ማግኘታቸውን ተናግሯል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከታች ላሉ ተማሪዎች በማሰብ የዚህ ዓይነት ሥልጠና በመስጠቱ ሊመሰገን ይገባል ያለው ተማሪው በቀጣይም ሰፋ ያለ ጊዜ ተሰጥቶ መሰል ሥልጠናዎች ቢዘጋጁ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር ይበልጥ ስለሚያስተዋውቁን ተጠናክረው ቢቀጥሉ ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት