የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት በነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሥራ አፈፃፀምና ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ከነፃ የሕግ ድጋፍ ማዕከላት አስተባባሪዎችና ከት/ቤቱ መምህራን ጋር የካቲት 12/2014 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በቅርቡ በነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ከደቡብ ክልል ፍትሕ ቢሮ የተገኘው ዕውቅናና ሽልማት በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ይበለጥ ለማጠናከርና የተሻለ አፈፃፀም እንዲመዘገብ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመው ውጤቱ እንዲመዘገብ ለሠሩ የት/ቤቱ መምህራን፣ ዲኖች፣ ለማዕከላት አስተባባሪዎችና ለት/ቤቱ ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባባሪያ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ት/ቤቱ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የጀመራቸው የትብብር ሥራዎች ይበለጥ ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው የጠቆሙት ዶ/ር ተክሉ እንደ ዩኒቨርሲቲም በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት ዲን አቶ እንየው ደረሰ በበኩላቸው ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የፍትሕ ተደራሽነትንና በዕኩልነት ፍትህ የማግኘት መብቶች በተግባር እንዲረጋገጡ እየተሠራ ያለውን ሥራ መደገፍን፣ በኢኮኖሚ አቅም ምክንያት ከፍለው ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን ማስከበር ለማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያንን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግን፣ በሕግ ትምህርት ውስጥ ተማሪዎች ከሚያገኙት የንድፈ-ሃሳብ ትምህርት ባሻገር በተግባር በአገልግሎቱ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ የተሟላ ዕውቀት፣ ክሂሎትና አመለካከት ያላቸው የሕግ ምሩቃንን ማፍራትን ዓላማ በማድረግ እየተሰጠ ያለ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አገልግሎቱን ይበለጥ ተደራሽ ለማድረግ ከተለያዩ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ዲኑ በቀጣይም በሰላም በር፣ ካምባ፣ ገረሴ፣ ቦረዳ፣ ደምባ ጎፋ፣ ኩልሜ፣ ፋሻ፣ ገዋዳና ኦላንጎ ተጨማሪ ማዕከላትን ለመክፈት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የሕግ ት/ቤት ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ወርቁ ፍትሕ የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ አቅም ለሌላቸዉ ዜጎች እና ቡድኖች የሕግ ድጋፍ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ቢሆንም እንደ አገር ያሉት የድጋፍ አማራጮች ትኩረት የተነፈጋቸው፣ ተደራሽ ያልሆኑ እና ያልተደራጁ መሆናቸውን ጠቁመው ይህንን ክፍተት ለመሙላት በማለም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መስጠት የሚያስቸለውን የጥብቅና ፈቃድ ግንቦት 2004 ዓ/ም ከደቡብ ክልል ፍትሕ ቢሮ በማግኝት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ አገልግሎቱን የጀመረው በጋሞ አካባቢ ከፍተና ፍርድ ቤት በከፈተው ማዕከል መሆኑን ያስታወሱት አቶ ዳኛቸው በአሁኑ ሰዓት በጫሞ ካምፓስ የሕግ ት/ቤት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ በአርባ ምንጭ ከተማ ፍርድ ቤት፣ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፍርድ ቤት፣ በአርባ ምንጭ ማረሚያ ተቋም፣ በጨንቻ፣ በብርብር (ምዕራብ ዓባያ)፣ በዋጫ፣ በሳውላ፣ በኮንሶ እና በጊዶሌ ማዕከላት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የሕግ ምክር አገልግሎት፣ ለፍርድ ቤትና ለአስተዳደር አካላት የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ማለትም ክስ፣ መልስ፣ ይግባኝ፣ የሰበር አቤቱታና የመሳሉትን መጻፍ፣ ወክሎ መከራከር እና ማስታረቅ በማዕከላቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን አገልግሎት የሚሰጠው በዋናነት ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ በማድረግ ሲሆን ሕፃናት፣ ሴቶች፡ አካል ጉዳተኞች፣ አቅመ ደካሞች፣ የሕግ ታራሚዎች እንዲሁም ከኤች አይ ቪ/ኤድስ ጋር አብው የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የአገልግሎቱ ዋነኛ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
በአገልግሎት አሰጣጡ የእስካሁን አፈፃፀም የታዩ ክፍተቶችንና የገጠሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በቀጣይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ በውይይቱ አጽንኦት የተሰጠው ሲሆን የተጀመሩ የትብብር ሥራዎችን ማጠናከር፣ ሥራ ላይ ያሉ ማዕከላትን ማጠናከር እንዲሁም አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ተጨማሪ የአግልግሎት መስጫ ማዕከላትን መክፈት እንደሚገባ በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡
በዕለቱ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሥራ እንዲጀመርና አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ የአመራርነት ሚናቸውን ለተወጡት የት/ቤቱ የቀድሞ ዲን ረ/ፕ ደርሶልኝ የኔአባት ከት/ቤቱ መምህራን የተዘጋጀ የምሥጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡