የሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት የፋይዳ ዳሰሳ ጥናት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የካቲት 14/2013 ዓ/ም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ፕሮጀክቱ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ በቀደሞው ጋሞ ጎፋ ዞን፣ በUniversity of Applied Sciences and Arts of Southern Switzerland እና በሳሃይ ሶላር ማኅበር እ.ኤ.አ በ2015 በተፈረመ የትብብር ስምምነት መሠረት የተከናወነ ሲሆን በእስከ አሁን ቆይታው 23 ጤና ጣቢያዎችንና 6 ት/ቤቶችን የ24 ሰዓት የፀሐይ ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ማድረጉ በዳሰሳ ጥናቱ ተመልክቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በመክፈቻ ንግግራቸው ሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት የገጠር ጤና ጣቢያዎችንና ት/ቤቶችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የእናቶችንና የሕፃናትን ሞት ከማስቀረት እንዲሁም ተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ከማድረግ አንፃር የጎላ ሚና የተጫወተ በመሆኑ ከዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች መካከል የምንኮራበትና ሌሎችም እንደ ትልቅ ልምድ የሚወሰዱት ነው ብለዋል፡፡ በፕሮጀክቱ እንደ ችግር የተነሳው የዘላቂነትና የባለቤትነት ጉዳይ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ለፕሮጀክቱ ቀጣይነትም ሆነ ሌሎች በአፈፃፀም ወቅት የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው የዞን ከፍተኛ አመራሮች ጋር እንሠራለን ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በፕሮጀክት ደረጃ የሚያከናውናቸው የተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት፣ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትና ሥልጠና፣ የአካባቢና አረንጓዴ ልማት ሥራዎች ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡ በሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት አማካኝነት የተከናወነው የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራ ውጤታማ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ተክሉ ፕሮጀክቱን በተሻለ መልኩ ለማስቀጠልም ሆነ ሌሎች መሰል ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ትምህርትና ልምድ የተገኘበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የታዳሽ ኃይል ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሶዴሳ ሶማ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ በ2009 ለዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች በሶላርና በታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት እንደተጀመረ አስታውሰው በነበረው የሙከራ ጊዜ 8 ት/ቤቶችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ፕሮጀክቱ በይፋ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጋሞና ጎፋ ዞኖች የሚገኙ 23 ጤና ጣቢያዎችንና 6 ት/ቤቶችን የ24 ሰዓት በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ አጠቃላይ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ ከ21 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከአቅም ግንባታ አንፃርም ለ300 የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች በ‹‹Basic Solar Photovoltaic Technology›› ዙሪያ እንዲሁም በአራት ዙር ለ200 የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች በሶላር ቴክኖሎጂ ዙሪያ አድቫንስድ ሥልጠና ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

የፕሮጀክት ፋይዳ ዳሰሳ ጥናት ሪፖርቱን ያቀረቡት መ/ር ስለሺ አበበ ፕሮጀክቱ ከ5 መቶ ሺህ በላይ በጤና ጣቢያዎች የሚገለገሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንዲሁም በትምህርቱ ዘርፍ 2,500 ተማሪዎችንና 80 መምህራንን ተጠቃሚ ማድረጉን

ተናግረው ፕሮጀክቱ የታለመለትን ዓላማ ሙሉ በሙሉ ያሳካ መሆኑን በዳሰሳ ጥናቱ ማረጋገጣቸውንም ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥና የደንበኞችን እርካታ ማሻሻሉን እንዲሁም በተቋማቱ በሚሠሩ ሠራተኞች ዘንድ መነሳሳትን፣ ቁርጠኝነትና የቆይታ ጊዜን የጨመረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የወጣው 21.7 ሚሊየን ብር ከፕሮጀክቱ የሥራ ስፋትና ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር አነሰተኛ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ስለሺ ይህም ፕሮጀክቱ ከሀብት አጠቃቀም አንፃር ውጤታማ እንደሆነ ያመላክታል ብለዋል፡፡

በባለድርሻ አካላት መካከል የተግባቦትና የግንኙነት ሂደት ደካማ መሆን፣ የክትትልና ድጋፍ ማነስ፣ የሥራ ኃላፊዎች በየጊዜው መቀያየር፣ በግልጽ የተቀመጠ የዘላቂነትና የባለቤትነት ሥርዓት አለመዘርጋት፣ የግብዓት እጥረት ወዘተ የፕሮጀክቱ ችግሮች መሆናቸው በጥናቱ መረጋገጡን የጠቆሙት አጥኚው ለችግሮቹ መፍትሔ የሚሆኑ ሃሳቦችን በጥናቱ ማስቀመጣቸውንም ተናግረዋል፡፡በቀረበው የፋይዳ ጥናት ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡