የዩኒቨርሲቲው የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ት/ቤት ለ2014 ዓ/ም አዲስ ተቀጣሪ መምህራን ከየካቲት 7-11/2014 ዓ/ም መሠረታዊ የማስተማር ሥነ-ዘዴ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
ሥልጠናው የትምህርት ዕቅድ አዘገጃጀት፣ የክፍል ውስጥ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አጠቃቀም፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሥነ-ምግባር ሕጎች፣ የክፍል አያያዝና ቁጥጥር፣ የትምህርት ምዘናና ተማሪ ተኮር የማስተማሪያ ሥነ-ዘዴ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ት/ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ ከተቋሙ ተልዕኮ አንዱ የመማር ማስተማር ሥራ በመሆኑ በየዓመቱ መሰል የአቅም ግንባታ ሥልጠና የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው ሥልጠናው የመምህራኑን የማስተማር አቅም በማጎልበት ለተማሪዎቹ በብቃት ዕውቀታቸውን ማስተላለፍ እንዲችሉ በማለም የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

ትምህርት ለግለሰብም ሆነ ለአገር ሁለንተናዊ ለውጥ ቁልፍ ሚና አለው ያሉት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ዕውቀትን በመላበስ አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ መማር እውነተኛነት፣ አርቆ ማሰብ፣ ታጋሽነት፣ ምክንታዊነትና ሳይንስን ተግብሮ ሕይወትን መቀየሪያ እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ር ዓለማየሁ ብቁ ዜጋን ለማፍራት ብቁ መምህር መሆንን የሚጠይቅ በመሆኑ ጥሩ ዝግጅት፣ በቂ ዕውቀትና የማስተማር ክሂሎት እንዲሁም ተገቢ የሆነ ስብዕና መላበስ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ት/ቤት መምህርና አሠልጣኝ አቶ ግርማ ጉራ ሠልጣኞች ከሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነት ባሻገር ያላቸውን ዕውቀት በምን መልኩ ማስተላለፍ እንዳለባቸው ማሳየት የሥልጠናው አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው የተለያዩ የምዘና ሂደቶችን የሚገነዘቡበትም ነው ብለዋል፡፡
ሌላኛው የት/ቤቱ መምህርና አሠልጣኝ ዶ/ር ቾምቤ አናጋው በመማር ማስተምር ሂደት ውስጥ የማስተማር ዘዴን ማወቅ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰው መምህሩ ተማሪ ተኮር የማስተማሪያ ዘዴን ተገንዝቦ መተግበሩ ተማሪው ትምህርቱን ተነቃቅቶና ተደስቶ እንዲማር መነሳሳትን ይፍጥርለታል ብለዋል፡፡ ከዚህም አንፃር ሠልጣኞች ከሥልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ በመጠቀም ተማሪ ተኮር የማስተማር ሥነ-ዘዴን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡

ሠልጣኞች ሥልጠናው ከአካዳሚክ ሙያችን ጋር አብሮ የሚሄድ፣ እንደ ከፍተኛ ት/ት ተቋም መምህር በመማር ማስተማር ሂደት ምን መተግበር እንዳለብን ያሳወቀን እና የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚያነሳሳና ውጤታማ እንድንሆን የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
በሥልጠናው ማጠቃለያ ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡