የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው በትምህርት ጥራት ዙሪያ ዋና ዋና ችግሮችን ለይቶ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የካቲት 25/2014 ዓ/ም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ማኅበረሰብ አባላት፣ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም ከተለያዩ ዘርፎች የተወጣጡ ተወካዮች በተገኙበት ባደረጉት ስብሳባ ገልጸዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ባለፉት 45 ዓመታት ውስጥ የትምህርት ሥርዓቱ በተጨባጭ ያለበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑ አንጻር የተለያዩ ጥናቶችንና ውይይቶችን በማካሄድ አራት ዋና ዋና ችግሮችን መለየት ተችሏል ብለዋል፡፡ ለትምህርት ሥርዓቱ መውደቅ መሠረታዊ ከሆኑ ችግሮች መካከል፡- የትምህርት ጥራት መውደቅ፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ የትምህርትና የክልልተኝነት መያያዝ እና የሞራል ኪሣራ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ጠቁመው በቀጣይ 5 ዓመታት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም በቀጣይ አዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን የመክፈትና የማስፋፊያ ግንባታዎች የማካሄድ ዕቅድ የሌለ ሲሆን በሂደት ላይ ያሉ ግንባታዎችን የማስጨረስ፣ ያለውን ግብዓት የማሻሻልና ጥራት የማስጠበቅ ሥራ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከታችኛው የክፍል ደረጃ ጀምሮ መሥራት ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ ከያዝነው የትምህርት ዘመን ጀምሮ የፈተና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ፈተናው በታብሌት እንዲሰጥ እየተሠራ ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከ50% በታች የሚያመጡ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊገቡ አይችሉም ብለዋል፡፡ እስከ አሁን ባለው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና መቁረጫ 34% መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር የቀጣዩ ትውልድ አብሮ የመኖርን፣ የመከባበርንና መተሳሰብን እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትን ለማዳበር ይረዳ ዘንድ 50 አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት፤ ከሁሉም ክልሎች በ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን በመግቢያ ፈተና ውጤት አወዳድሮ በመቀበል እንዲማሩ የሚደረግ ሲሆን በ2016 ዓ/ም 13ቱ ትምህርት ቤቶች ተጠናቀው ሥራ ላይ እንደሚውሉ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲዎች ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው የእውነትና የእውቀት ምንጭ እንዲሆኑ ለማስቻል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዳደር ቦርድ አወቃቀር ጀምሮ ያለው ሥርዓት ሁሉን ባማከለ መልኩ መደራጀቱን እና በቅርብም ተግባራዊ እንደሚደረግ የጠቆሙት ሚኒስትሩ ሁሉም ባለድርሻዎች በጋራ ለለውጥና የተሻለ ትውልድ ለማፍራት እንዲተጉ ጠይቀዋል፡፡

የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፈንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው እንደገለጹት መጪው ትውልድ የተሻለ ሀገር እንዲኖረው የሚያስችለውና የሀገራችንን እጣ ፈንታ የሚወስነው ትምህርት እንደመሆኑ ትውልድን የሚቀርጹ መ/ራን የሚገባቸውን የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ክፍያ እንዲሁም የሙያ ክብር እንዲያገኙ ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር ያሉብንን ተቋማዊ ክፍተቶችን ሞልተን አስተወጽኦ ማድረግ የምንችለው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምንሠራቸው ሥራዎች ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በቸልተኝነት ተማሪዎች የሚገባቸውን ሳያውቁና በቂ ክሂሎት ሳያገኙ እንዲመረቁ ማድረግ የትምህርት ሥርዓትን መግደል ነው ብለዋል፡፡

ከ2015 ዓ/ም ጀምሮ ሁሉም የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች ተመርቀው ሲወጡ የሚሰጣቸውን የመውጫ ፈተና በማለፍ ብቻ ሥራ መቀጠር የሚችሉ ሲሆን በመጀመሪያ ዙር ፈተና ካለለፉ በስድስት ወራት ልዩነት ሁለት ጊዜ በግል መፈተን የሚችሉ እና በሦስቱም ዙሮች ፈተና ያላለፉት ደግሞ በመስኩ መቀጠር የማይችሉ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አክለው ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደገለጹት አዲሱ የትምህርት ፍኖተ-ካርታ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሆነ በአጠቃላይ ትምህርት ደረጃ ከየትኛውም የመንግሥት ሥርዓት ጋር የሚቀየርና የሚሻሻል እንዲሁም ከየትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ጋር የሚቃኝ ሳይሆን ሀገሪቱንና ዜጎቿን ታሳቢ ያደረገ የሰው ልጅን የመማር፣ የመላቅ አቅምን ባገናዘበ ሁኔታ ሀገሩን አውቆና ግብረ ገብነት ተላብሶ እንዲሄድ ለማድረግ ብርቱ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት