የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማስተባበሪያ ማዕከል ‹‹አፍሪካን - ኢትዮጵያን ከምዕራባዊያን ተጽዕኖ እንዴት ነፃ እናድርጋት?›› በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም የካቲት 24/2014 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዕለቱ የክብር እንግዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሚኒስቴር መ/ቤታቸው የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም፣ ነጻነትንና ሉዓላዊነትን ለማስከበር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎችን ቀርጾ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ በዜጋ ተኮርና የሀገር ገጽታ ግንባታ ሥራዎች ላይ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ተልዕኮው እንዲሳካ ‹ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ዲፕሎማት ነው› የሚለውን መርህ በመከተል ዜጎች በያሉበት ለሀገራቸው የሚቻላቸውን እንዲያበረክቱ ሥርዓት ዘርግቷል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከላትን በማቋቋም የውጭ ግንኙነት ሥራዎችን በሳይንስና ምርምር አስደግፎ ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ ሥራዎችን ለመሥራትና በሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የዓለማችን ኃያላን ሀገራት ፍላጎቶቻቸውን ከሚያስፈፅሙባቸውና ተጽዕኖዎቻቸውን ለማሳደር የዲፕሎማሲ ተቋሞቻቸውንና ዲፕሎማቶቻቸውን የሚጠቀሙ መሆኑን ጠቅሰው በኢትዮጵያም የኃያላኑን ጫናና ተጽዕኖ መቋቋም የሚያስችሉ ተቋማትን ማደራጀትና ያሉትንም ፈትሾ ማጠናከር አስፈላጊ ነው፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገር ዲፕሎማሲ ሥራ ላይ መሳተፋቸው ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የጠቀሰት ፕሬዝደንቱ በሀገራችን የዲፕሎማሲ ፖሊሲና አተገባበር ላይ ያሉ ጥንካሬዎችንና ድክመቶችን በመፈተሽ የተሻለውን የፖሊሲ አማራጭና ውጤታማ አካሄድን ማመላከት ከዘርፉ ምሁራንና ተመራማሪዎች የሚጠበቅ ሀገራዊና ሞራላዊ ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ዓለማየሁ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ጥቅም ለማስከበር የዲፕሎማሲ ተቋማትን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መነሻ የሚሆን የጋራ ውይይት ለማድረግ ሲምፖዚየሙ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በየተቋሞቻችን የሀገራችንን ታላላቅ አጀንዳዎች በመውሰድ የዲፕሎማሲ ተቋማት የሚጠናከሩበትን መንገድ መቀየስና እንደ ዜጋ የሚጠበቅብንን ሁሉ መወጣት ይገባናል ብለዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ ‹‹የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ዓለም አቀፍ አስተዳደር፡- የጸጥታው ምክር ቤት ሚና››፣ ‹‹ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በዓለም አቀፍ የሕግ ቻርተር ሲታይ››፣ ‹‹አፍሪካ በሌላው ዓለም፣ በምዕራባዊያንና ምዕራባዊ ባልሆኑ መካከል ያላት ቦታና ሁለንተናዊ ግንኙነት›› የሚሉ ጥናታዊ ጽሑፎች በተመራማሪዎች ቀርበዋል፡፡

ሲምፖዚየሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲን ጨምሮ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ አመራሮችና ተመራማሪዎች፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የጋሞ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪዎች ታድመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት