ከ9 ሺህ በላይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባት ከነገ የካቲት 30/2014 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ 3 ቀናት እንደሚሰጥ ተገለጸ፡፡ በክትባቱ አሰጣጥና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል ዛሬ የካቲት 29/2014 ዓ/ም መክሯል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በውይይቱ ላይ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ሁለት ዓመት እየሞላው መሆኑን አስታውሰው ቫይረሱን ለመከላከል እየተተገበሩ ካሉ ዘዴዎች መካከል ለቫይረሱ መከላከል እየተሰጡ ያሉ ክትባቶች በሽታውን ከመከላከል አንፃር የተሻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ክትባቱ በበሽታው የመያዝ ዕድልን ከመቀነሱ ባሻገር በቫይረሱ ብንያዝ እንኳን የሕመም መጠንን እንደሚቀንስና ሞትንም እንደሚያስቀር ዶ/ር ታምሩ ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ በአርባ ምንጭ፣ ዲላና ሀላባ ከተሞች ባደረገው የዳሰሳ ጥናት በከተሞቹ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል 97 በመቶው ክትባቱን ያልወሰዱ መሆናቸው እንዲሁም በቫይረሱ ከሞቱ ሰዎች መካከል ሁሉም ክትባቱን ያልተከተቡ መሆናቸውን ያመላክታል ያሉት ዶ/ር ታምሩ ይህም የክትባቱ ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

በማኅበረሰቡ ዘንድ የቫይረሱን ክትባት የመውሰድ ፍላጎት አነስተኛ ሲሆን ይህም በክትባቱ ዙሪያ በተሰራጩ የተዛቡ መረጃዎች ምክንያት መሆኑን ዶ/ር ታምሩ ጠቁመዋል፡፡ ለኮሮና ቫይረስ ተብለው የተዘጋጁ ክትባቶች የተዘጋጁበት አሠራርም ሆነ አመጣጥ ሌሎች ክትባቶች ከተሠሩበት መንገድም ሆነ አሠራር የተለየ አለመሆኑንና ክትባቱን ከተለያዩ መንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር ማያያዝም ተገቢ አለመሆኑን ዶ/ር ታምሩ ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም መላው የዩኒቨርሲቲያችን ማኅበረሰብ በየካምፓሱ በሚገኙ ክሊኒኮች በመገኘት ክትባቱን በመውሰድ የራሱን፣ የቤተሰቡንና የአካባቢውን ብሎም የማኅበረሰቡን ጤና እንዲጠብቅ አሳስበበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ አሁን ድረስ የዓለም የጤና ስጋት መሆኑን ተናግረው በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች ያለው የአኗኗር ዘይቤ ይበልጥ ለቫይረሱ ተጋላጭ ያደርገናል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ቫይረሱን ለመከላከል ሲደረጉ የነበሩ ጥንቃቄዎች በእጅጉ እየቀነሱ ናቸው ያሉት ዶ/ር ዳምጠው ከዚህም አንፃር ክትባት መውሰድ የተሻለ የመከላከያ መንገድ መሆኑን በመገንዘብ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የተገኘውን ዕድል በመጠቀም ክትባቱን እንዲውስድ አሳስበዋል፡፡

በክትባቱ ዙሪያ የሚስተዋሉ የአመለካከት ችግሮችን ለመቅረፍ በተለይ የጤና ባለሙያዎች በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ያሳሰቡት ዶ/ር ዳምጠው ከነገ ጀምሮ የሚጀመረው የክትባት ዘመቻ እንዲሳካ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የሥራ ክፍል ኃላፊዎችና አስተባባሪዎች የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡

የክትባት ዘመቻው በጋሞ ዞን ጤና መምሪያ፣ በአርባ ምንጭ ጤና ጽ/ቤትና በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን ከነገ የካቲት 30/2014 ዓ/ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች በሚገኙ ኪሊኒኮች ይሰጣል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት