የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ከኮንሶ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ጋር በመተባበር ለፍ/ቤቱ ዳኞች፣ ሬጂስትራሮችና ዐቃቤያን ሕግ የወንጀል፣ የውልና ከውል ውጪ ኃላፊነቶች ሕግ ላይ ከመጋቢት 01/2014 ዓ/ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የወንጀል ሕግ ምንነት፣ ዓላማ፣ መርሆዎችና አፈፃፀም፣ የወንጀል ተሳትፎ ደረጃ፣ የወንጀል ተጠቂዎች/ተበዳዮች የሚካሱበት መንገድ፣ የውል ሕግ፣ የውል አፈፃፀም፣ የውል አፈፃፀም መብትና ግዴታዎች፣ የዋስትና ውል እንዲሁም ከውል ውጭ ኃላፊነት ሕግ በሥልጠናው የተካተቱ መሆኑን የሕግ ት/ቤት ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ወርቁ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ዳኛቸው የውል ሕግ ሰዎች በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ የሚፈጥሩት ግንኙነት አስተማማኝ እንዲሆንና በንብረቶቻቸው ላይ ያላቸው መብቶች ዋስትና እንዲያገኙ የልውውጡን ሥርዓት የሚገዛና በልውውጡ ሂደቶች የሚኖሩ ግንኙነቶችን የሚያስተዳድር ነው፡፡ ሕጉን በተመለከተ ሥልጠናው የፌዴራል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ውሳኔዎችን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ውል በሚጣስበት ጊዜ መፍትሔዎቹ፣ ተዋዋይ ወገኖች በቁጥር ብዙ በሚሆኑበት ጊዜ የውል አፈፃፀም፣ የሚኖርባቸው ኃላፊነትና መብታቸውን የሚያስጠብቁበት መንገድ እንዲሁም የዋስትና ውልና አጠቃላይ የውል ጉዳዮችን የሚዳስስ ነው፡፡

ሌላው በፍ/ቤቶችና በሕግ ባለሙያዎች ዘንድ የተዘነጋና ብዙም የማይሠራበት ነገር ግን ወሳኝ የሆነው ከውል ውጭ ኃላፊነት ሕግ ነው ያሉት አቶ ዳኛቸው ከስምምነት ውጪ ያሉ ግንኙነቶች ላይ አንድ ሰው ጉዳት ቢደርስበት መፍትሔና ካሳ የሚያገኝበት የሕግ ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ርዕሰ ጉዳዮቹን አስመልክቶ ሥልጠናው ዳኞችና ዐቃቤያን ሕግ በተለይም አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ እንደሚያሳድግ አቶ ዳኛቸው ተናግረዋል፡፡

የወንጀል ሕግን አስመልክቶ ሥልጠና የሰጡት የሕግ ት/ክፍል ኃላፊና አሠልጣኝ አቶ ጎድሴንድ ኮኖፋ የወንጀል ሕግ በሀገራችን ፍትሕን ለመስጠት ከወጡት ሕጎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በፍ/ቤቶች የአሠራር ሂደት በተለይ የወንጀል ተጠቂ የሆኑ ሰዎች የሚካሱበትን ሕግ ተፈፃሚ ከማድረግ አኳያ በቂ ትኩረት አለመስጠትና ሌሎችም ክፍተቶች መኖራቸውን ከሠልጣኞች ጋር ባለው የሃሳብ ልውውጥ ተረድተናል ብለዋል፡፡ በሥልጠናው ተግባራዊ ተሞክሮዎች፣ ውሳኔ ያገኙ አከራካሪ መዝገቦችና የተሻሻሉ ሕጎችን በማንሳት ሰፊ የልምድ ልውውጥ መደረጉን አቶ ጎድሴንድ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ማኅበረሰብ ወቅቱንና ደረጃውን የጠበቀ ፍትሕ እንዲያገኝ ለማስቻል የፍትሕ አካላትን በማሠልጠን ማብቃት የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት እንደ ኃላፊነት የሚወስደው መሆኑን የገለጹት አቶ ጎድሴንድ ከሠልጣኞች ለተማሪዎቻችን ማስተማሪያ የሚሆኑ ተግባራዊ ነጥቦችንም አግኝተናል ብለዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት ዲን አቶ እንየው ደረሰ እንደገለጹት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ከምሥረታው አንፃር አጭር ጊዜያትን ያስቆጠረ ቢሆንም በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች አንጋፋ ከሚባሉት ት/ቤቶች

የተሻሉ ሥራዎች እያከናወነ ነው፡፡ በመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም የሴክሽን ቁጥር ማሳደግ፣ ተጨማሪ የ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን መክፈት፣ የነፃ የሕግ ድጋፍ ማዕከላትን ማስፋፋት፣ አጫጭር ሥልጠናዎችን በስፋት መስጠት እንዲሁም የት/ቤቱ መምህራን በቡድን ፕሮጀክቶችን በማምጣት ለማኅበረሰቡ የሚበጁ ተግባራትን ማከናወን ተጠቃሽ ሥራዎች መሆናቸውን አቶ እንየው ተናግረዋል፡፡

የኮንሶ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የባለሙያዎቹን የክሂሎት ክፍተትና ርዕሰ ጉዳዮችን ለይቶ የሥልጠና ጥያቄ ማቅረቡና የፍትሕ አስፈፃሚዎችን አቅም ለመገንባት ያለው ተነሳሽነት በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ያሉት አቶ እንየው ፍ/ቤቶች በተጻፈ ሕግ እንደመተዳደራቸው ውሳኔዎቻቸው ቸልተኛና ከሕግ ያፈነገጡ እንዳይሆኑ ዳኞችና ዐቃቤያን ሕግን ከማንቃትና የሕግ ጽንሰ ሃሳቦችን ከማስታወስ አንፃር ሥልጠናው ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም አሠልጣኝ መምህራኑ በሚያሠለጥኑት ርዕሰ ጉዳይ ላይ በቂ ዕውቀት ያላቸውና በየርዕሰ ጉዳዮቹ ዓለም ዓቀፍ አሠራሮች፣ ልምዶችና አዳዲስ ሕጎች የሚዳሰሱ በመሆኑ ሠልጣኞቹ ነባር ዕውቀታቸውን የሚያዘምኑበትና አሠራራቸውን የሚቃኙበት ነው ብለዋል፡፡

በሥልጠናው የተካተቱት ርዕሰ ጉዳዮች ከፍ/ቤቱ የዕለት ከዕለት መዝገቦች ውስጥ የማይጠፉ በመሆናቸው እንዲሁም መጠይቆችን በማዘጋጀት የሠልጣኞችን ፍላጎት በመለየት የተመረጡ መሆኑን የኮንሶ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዝደንት አቶ ሙሃባ ቃውያ ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው ፍትሕን በማስፈጸም ሂደት በተግባር የሚያከናውኑት በሕግ ከተቀመጠው ጋር የማይጣረስ መሆኑን የሚፈትሹበት ነውም ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ መንግሥት ፍትሕ ቢሮና በክልሉ በሚገኙ 7 ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በጋራ በተከናወኑ የፍትሕና የሕግ አገልግሎት ሥራዎች የላቀ አፈጻጸም በማስመዝገብ በቅርቡ የእውቅናና የዋንጫ ሽልማት ማግኘቱ የሚታወስ ነው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት