የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት በዓለም ለ111ኛ በሀገራችን ለ46ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ‹‹እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ›› በሚል መሪ ቃል መጋቢት 01/2014 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣መምህራን፣ ሴት የአስተዳደር ሠራተኞችና ሴት ተማሪዎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ አክብሯል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንቱ ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የሴት ልጅ ጥቃት ችግሮች የሚበዙት የሰው ልጅ አስተሳሰብና ንቃተ ሕሊና ዝቅ ሲል መሆኑን ተናግረው ዕውቀት የሰውን አዕምሮና አስተሳሰብ ለመቀየር ወሳኝ መሳሪያ በመሆኑ ከሴቶች ጥቃት ለመውጣት በትምህርት ጥሩ ስብዕና ያለው ትውልድ መፍጠር ግድ ነው ብለዋል፡፡

ከቀደሙት ዓመታት አንፃር ሲታይ የሴቶችን ጥቃት ከመቀነስ አልፎ እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሠሩ በመሆኑ በርካታ ሴቶች ከዝቅተኛ ሥራ ጀምረው እስከ ሚኒስትርነትና ርዕሰ ብሔርነት መድረሳቸውን ዶ/ር ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ስኬቶች ሴቶች የትኛውም ቦታ መሥራት እንደሚችሉ ማሳያ ይሁኑ እንጂ ችግሩ ተፈቷል ለማለት የማያስደፍሩ በመሆናቸው ሙሉ በሙሉ እስኪጠፉ ሁላችንም የበኩላችንን ኃላፊነት ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ እንደገለጹት በዓሉ የሚከበርበት ዋነኛ ዓላማ በዓለም ያሉ መንግሥታት የሴቶች ጉዳይ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ጉዳይ እንደሆነ አምነው በመቀበል በሴቶች ዙሪያ ፖሊሲዎቻቸውን፣ ሕጎቻቸውንና አሠራሮቻቸውን በመፈተሽ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ መድልኦዎችን እንዲያስወግዱና የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ለማነሳሳት ነው፡፡

አክለውም ሴቶች በድንበር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም፣ በቋንቋና በባህል ሳይለያዩ የሚደርስባቸውን ጭቆናና መድልኦ የሚያወግዙበት፣ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት፣ ድምጻቸውን በጋራ የሚያሰሙበት፣ ለነፃነት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት ያደረጉትን ተጋድሎ የሚዘክሩበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበትና ለበለጠ ትግል ተቀናጅተው ቃል የሚገቡበት ነው ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ባቀረቡት ሰነድ ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ከ“INBAR” ፕሮጀክት ጋር በጋራ በመሥራት በሴቶች የሚመሩ 3 ኢንተርፕራይዞችን አደራጅቶ 2ቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው መምህርት ተ/ፕ ግስታኔ አየለ ሴቶች በኢትዮጵያ ባህል የሥራ ጫና ያለባቸው ቢሆንም በተቻለ መጠን ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀምና በራስ የመተማመን ብቃታቸውን በማጎልበት የሚደርስባቸውን ጫና በትጋትና በፅናት ተቋቁመው ወደ አንድ ዓላማ መድረስ እንደሚችሉ ልምዷን አካፍላለች፡፡

ሌላኛዋ የዩኒቨርሲቲው መምህርት ረ/ፕ ገሊላ ቢረሳው በበኩሏ በተሰማራንበት ሁሉ ስኬታማ ለመሆን በዓላማ መቆም፣ ቆራጥ መሆንና ፅናት አስፈላጊ በመሆኑ ሴቶች በራስ የመተማመንና እችላለሁ የሚል ስሜት ሊኖረን ይገባል ብላለች፡፡

የዩኒቨርሲቲው አመራሮችም ሴቶችን ማበረታታት፣ እንደምትችል መናገርና ማገዝን በተግባር ማሳየት እንዳለባቸውም ተናግራለች፡፡

የ3ኛ ዓመት የፎረንሲክ ኬሚስትሪ ተማሪ ሃና ይገዙ የሴቶች ቀን በመከበሩ ደስተኛ መሆኗን ገልጻ በዓሉን ማክበር ብቻ ሳይሆን በየአጋጣሚዎቹ የመሥራት አቅምና ጥንካሬያችንን ማሳየት አለብን ብላለች፡፡ ሴት ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታዎች ሳያባክኑ ዓላማቸው ላይ ትኩረት አድርገው ከሠሩ ስኬታማ መሆን እንደማያቅታቸውም ተናግራለች፡፡

ውይይት፣ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና ምላሾች፣ መነባንብ የፕሮግራሙ አካል ሲሆኑ ከየኮሌጆች ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ሴት ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በፕሮግራሙ ፍፃሜም በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየችው የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ጽጌረዳ ግርማይ የሕሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት