የዩኒቨርሲቲው የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝ/ት/ግ ዳይሬክቶሬት ከፌዴራል የትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የዕቅድ ባለሙያዎችና ለቡድን መሪዎች በዕቅድ አዘገጃጀት ዙሪያ ከመጋቢት 02-03/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዕቅድ አዘገጃጀትና አቀራረብ ጽንሰ ሃሳብ፣ አዲሱ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሪፖርት አቀራረብና ይዘት፣ የ10 ዓመት የተከለሰ የትምህርት ሚኒስቴር ዕቅድ፣ የ10 ዓመት የተናበበ የትምህርት ሚኒስቴር ዓመታዊ ዕቅድና ተያያዥ ጉዳዮች በሥልጠናው ተዳስሰዋል፡፡

የሥልጠናው ዓላማ የተቋማት መቀያየር የዕቅድ መለዋወጥን ስለሚፈጥር ትምህርት ሚኒስቴር እንደ ተጠሪ መሥሪያ ቤት ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተናበበ ዕቅድ እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቀረበው አዲስና ወጥ የሆነ የሪፖርት አቀራረብ ዙሪያ ግንዛቤን በመፍጠር የሚቀርቡ የሪፖርት መረጃዎች ተመሳሳይና የማይጣረሱ እንዲሆኑ ለማስቻልም ነው፡፡

የታቀደው ዕቅድ ከሀገራዊ ልማት ጋር እንደሚናበብ በመዳሰስ ዩኒቨርሲቲው ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ዕቅድ ተነስቶ ያቀደውን የ10፣ የ5ና የ1 ዓመት ዕቅድ በማቅረብ የማናበብ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ዕቅድን በአግባቡ ተረድቶ ማቀድ የሰው ሀብትን፣ በጀትንና ከአጋር ድርጅቶች ማግኘት የሚቻሉ ነገሮችን ተጠቃሚ ለመሆንና አቅምን አሟጦ ለሀገር ልማትና እድገት ለመጠቀም እንደሚያግዝ ተጠቁሟል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ሊለካ የሚችል አፈፃፀም ለማስመዝገብ ዕቅድ ሲዘጋጅ ሳይንሱንና መካተት ያለባቸውን ጠንቅቆ መረዳት እንደሚገባ ገልጸው በዕቅድ ሥራ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ሥልጠናው አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝ/ት/ግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስፋው ደምሴ እንደገለጹት ሥልጠናው በስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት፣ በሥራ አፈፃፀም ሪፖርት አቀራረብ፣ በግቦችና ቁልፍ የውጤት አመልካቾች (KPIs) መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ነው፡፡ እንደ ሥራ ክፍል የነበረውን የሥራ ብዥታ የሚቀንስ በመሆኑ ባገኙት ክሂሎት በመጠቀም የተሻለ ዕቅድ ለመንደፍና ሪፖርት ለማዘጋጀት የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት