9ኛው ዓመታዊ የምርምር ግምገማ ወርክሾፕ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች በተገኙበት ከመጋቢት 02-03/2014 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመክፈቻ ንግግራቸው በአዲሱ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መዋቅራዊ አደረጃጀት ምርምርን ከመማር ማስተማር ጋር ለማስተሳሰር አጽንኦት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዓለማየሁ የምርምር ግምገማ ወርክሾፑ ከተለያዩ የትምህርት ክፍሎችና ሙያ ዘርፎች የተወጣጡ የምርምር ሥራዎች የሚገመገሙበት፣ የተለያዩ የምርምር ችግሮች ለውይይት የሚቀርቡበት፣ የግራንድ ፕሮጀክት ሃሳቦች መነሻ የሚገኝበት እንዲሁም አዳዲስ ተመራማሪዎች የተሻለ ልምድ የሚያገኙበትና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚሰጡበት ነው፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ወርክሾፑ ሁሉም ኮሌጆች በየራሳቸው ሲያካሂዱ የቆዩት የምርምር ሥራዎች፣ የተመዘገቡ ሳይንሳዊ ግኝቶችና ውጤቶች የሚቀርቡበትና የሚገመገምበት ዓመታዊ ወርክሾፕ ነው ብለዋል፡፡

ም/ፕሬዝደንቱ በዩኒቨርሲቲው ምርምሮች ከተጀመሩ በኋላ በጊዜ ያለማጠናቀቅ ልማድ በተደጋጋሚ የሚስተዋል መሆኑን ጠቁመው ግምገማውም መሰል ችግሮች እንዲቀረፉና እንዳይደገሙ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የምርምር ሥራ ወቅቱ በሚፈልገው ሁኔታ እንዲከናወን የሚያስችል የምርምር መመሪያም ተከልሶ ተግባራዊ የተደረገ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ዩኒቨርሲቲው የትብብር ፕሮጀክቶችን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አሁን እስካለበት ድረስ የተገኙ ልምዶች የኅብረተሰቡን ሕይወትና የአካባቢውን ሁኔታ የሚቀይሩ የምርምር ፕሮጀክቶችን ለመቅረጽ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው ግራንድ የምርምር ፕሮጀክቶችን ቀርጸው የሚያመጡ ተመራማሪወችን የሚያበረታታና የሚደግፍ መሆኑን፣ በቀጣይ በሚከናወኑ የምርምር ትኩረቶችና ተግባራት ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ዶ/ር ተስፋዬ ከሌሎች የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሲነጻጸር በዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ ተጀምረው ከሚጠናቀቁና አዳዲስ ግራንድ የምርምር ፕሮጀክቶችን ከማስጀመር አንጻር በቀጣይ ብዙ መሥራት ይጠበቃል፡፡

‹‹A compendious Approach for Renewable Energy Assessment Based on Satellite and Ground Truth Data: Bilate Catchment Rift Valley Basin, Ethiopia››፣ ‹‹Incidence Predictors of Medication Errors Among Admitted in Public Hospitals of Gamo Zone, Southern Ethiopia›› እና ‹‹Valuation of Factors Influencing Farmers Adoptions of Sustainable Land Management Technology Practices: Case of Geze Gofa Woreda, Gofa Zone, Ethiopia›› በሚሉ 3 ርዕሶች የምርምር ጽሑፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ተገምግመዋል፡፡ ሌሎቹ የምርምር ሥራዎች በየካምፓሱ እንዲገመገሙ ተደርጓል፡፡

በግምገማው 78 የተጠናቀቁና በሂደት ላይ የሚገኙ የምርምር ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ በአጠቃላይ 235 የተጠናቀቁና 745 በሂደት ላይ ያሉ የምርምር ሥራዎችች በዳይሬክቶሬቱ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ ከነዚህም መካከል አሥራ አንዱ ግራንድ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት