የዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ በ‹‹Gamoththo Language and Literature››፣ በ‹‹Land use Planning and Policy Analysis››፣ ‹‹Federalism and Governance››፣ ‹‹Linguistics in English›› እና ‹‹Literature in English›› የ2ኛ ዲግሪ እንዲሁም በ ‹‹Social Anthropology›› የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ለመክፈት መጋቢት 6/2014 ዓ/ም ውጫዊ የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ እንደገለጹት የግምገማው ዓላማ የመርሃ-ግብሮቹን ደረጃ ለማስጠበቅ የሚረዱ ጠቃሚ መረጃዎችና አስተያየቶችን ከውጪ ገምጋሚዎችና ከተሳታፊዎች ማግኘት ነው፡፡ እንደ ዶ/ር ሙሉጌታ ኮሌጁ በተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር፣ በአደጋና ስጋት አስተዳደር እና እንግሊዝኛን እንደ ውጪ ቋንቋ በማስተማር እና ሌሎች ፕሮግራሞችን በ2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ መርሃ-ግብሮች ከፍቶ በማስተማር ላይ ሲሆን ካለው እምቅ አቅም አንጻር ተጨማሪ የትምህርት መርሃ-ግብሮችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ዶ/ር ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡

የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የአካ/ጉ/ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ እንደገለጹት የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚ ተግባር ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን ለማድረግ የሚያስችሉ የትምህርት ፕሮግራሞችን መቅረጽና ማስፋፋት እንደመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ጠንካራ ጥረት አድርጎ በአሁኑ ወቅት የ113 የ2ኛ እና የ25 የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች ቀርጾ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡

ዶ/ር ሠረቀብርሃን አክለውም ይህ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት መስፈርቶችን አሟልቶ ከጸደቀ የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ያለውን ፕሮግራሞች ከ11.9 ወደ 15.8 በመቶ ከፍ ያደርጋል፡፡ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት በትልቅ ኃላፊነት የሚሠራ ከመሆኑም ባሻገር ብዙ ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅ ሀገራዊ ኃላፊነትን የመሸከም ጉዳይ ነው ያሉት ዶ/ር ሠረቀብርሃን በዝግጅት ተግባሩ ላይ የተሳተፉትን መምህራንና ኃላፊዎችን አመስግነዋል፡፡

የእንግሊዝኛ ስነ-ጽሑፍን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ሥርዓተ-ትምህርት ያቀረቡት የትምህርት ክፍሉ መምህር ዶ/ር እንዳልካቸው ኃይሉ እንደገለጹት ሥርዓተ-ትምህርቱ በውስጡ የስነ-ጽሑፍ ንድፈ ሃሳቦችን፣ የስነ-ሂስ ዘዴዎችን፣ ከስነ-ልሳን ንድፈ ሃሳብ ጀምሮ ስነ-ጽሑፍን መተንተን፣ መረዳትና ማብራራት የሚችሉበትን ክሂሎት ለተማሪዎች የሚያስጨብጥ ነው፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ስነ-ጽሑፍ ላይ ከጥንት የግዕዝ ስነ-ጽሑፍ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለውን የሚዳስሱበት እንዲሁም ባህልና የተለያዩ እሴቶችን ተማሪዎች እንዲያውቁ የሚያስችሉ ኮርሶች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ በዝግጅቱም ከተለያዩ ዘርፎች 166 ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሥርዓተ-ትምህርቱ የውጪ ገምጋሚ የሆኑት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ ጽሑፍ ት/ክፍል መምህር ዶ/ር ብርሃኑ ማቴዎስ እንደገለጹት ሥርዓተ-ትምህርቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአዲስ ፕሮግራም ቀረጻ ውስጥ ያሉ ነጥቦችን መሠረት በማድረግ የተገመገመ ሲሆን አስፈላጊ ነጥቦችን በሙሉ የያዘ ቢሆንም የተሰጡ አስተያየቶች በቀጣይ ተካተው እንዲጸድቅ በግምገማቸው ጠቁመዋል፡፡

የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ሲከፈቱ ብዙ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ የተናገሩት የሶሻል አንትሮፖሎጂ ሥርዓተ ትምህርትን የገመገሙት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዳኜ ሽብሩ ት/ክፍሉ ያለውን ተነሳሽነት በሰው ኃይልና በመሠረታዊ ግብዓቶች ቢያጠናክር ጥሩ ውጤት ይመጣል ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ፕሮግራሙ ተግባራዊ የሚደረግበት መንገድ በሥርዓተ ትምህርቱ ሊካተት እንደሚገባ ብሎም ማስተካከያና ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው አሳስበዋል፡፡

የሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ት/ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ካሌብ ካሳ በሰጡት አስተያየት የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ በዝግጅት ቆይታው ብዙ ለውጦች እንደሚኖሩና የተነሱ ሃሳቦችንና አስተያየቶችን በመውሰድ ጥሩ የሆነ ሥርዓተ-ትምህርት እንደሚያዘጋጁ ተናግረዋል፡፡

በግምገማው ሂደት በሁሉም ፕሮግራሞች የቀረቡትን ሥርዓተ ትምህርቶች ይበልጥ ለማጠናከር የሚረዱ በርካታ ገንቢ አስተያየቶች ከተሳታፊዎች እና ከውስጥና ከውጪ ገምጋሚዎች ተሰጥተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት