የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከ12 ሆስፒታሎች ለተወጣጡ የጤና ባለሙያዎችና ሐኪሞች በ ‹‹Clinical Preceptorship›› ዙሪያ ከመጋቢት 5-7/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በመክፈቻ ንግግራቸው የሕክምናና ጤና ትምህርትና ሥልጠና በባህሪው ሰፋ ያለ የተግባር ልምምድ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረው በዋናነት ተማሪዎች በጤና ተቋማት የሚያሳልፉት የልምምድና ሥልጠና ጊዜ ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ዕውቀትና ክሂሎት እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ የጎላ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በሄዱባቸው የጤና ተቋማት በአግባቡ የልምምድ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ከማድረግ አንጻር በተቋማቱ የሚሠሩ ባለሙያዎች ሚና የጎላ ነው ያሉት ዶ/ር ታምሩ ሠልጣኞችም ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ክሂሎት በመጠቀም የተጣለባቸውን ብቁ የጤና ባለሙያዎችን የማፍራት ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኮሌጁ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ረ/ፕ ደስታ ሀብቱ የሥልጠናው ተሳታፊዎች የኮሌጁ ተማሪዎች የተግባር ልምምድ ከሚያደርጉባቸው 12 ሆስፒታሎች የተወጣጡ የነርሲንግ፣ ሚድዋይፍሪ፣ ላቦራቶሪ፣ አንስቴዢያ ባለሙያዎችና ሐኪሞች መሆናቸውን ተናግረው ሥልጠናውም በተማሪ አያያዝ፣ አስተዳደርና ምዘና ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር በቀጣይ ለተማሪዎች ምቹ የልምምድ አካባቢ ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኮሌጁ ለተማሪዎች የክሊኒካል ተግባር ትምህርት ውጤታማነት የተለያዩ ዘዴዎችን ቀይሶ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው በቅርቡ መሰል ሥራዎችን የሚያቀላጥፉ የትብብር መግባቢያ ስምምነቶችን ከተለያዩ የጤና ተቋማት ጋር መፈራረሙንም አውስተዋል፡፡

በኮሌጁ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪምና አሠልጣኝ ዶ/ር ኢየሩሳሌም በየነ ፕሪሰፕተርሺፕ የሕክምናና ጤና ተማሪዎች በሕክምና መስጫ ተቋማት ተገኝተው የተግባር ልምምድና ሥልጠና የሚያገኙበት የትምህርት ጊዜ መሆኑን ተናግረው በዚህ ክሊኒካዊ ልምምድ ወቅት ተማሪዎቹን ለሚከታተሉና የተግባር ሥልጠናዎችን ለሚሰጡ ሲኒየር ባለሙያዎችና ሐኪሞች (Preceptors) በኮሚየኒኬሽን ክሂሎት፣ በፕሪሰፕተርሺፕ መርሆችና ሌሎች ሙያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠናው ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከወላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል የመጣችው የአንስቴዢያ ባለሙያ መስከረም አብርሃም ከሥልጠናው ለተግባር ልምምድ ከሚመጡ ተማሪዎች አቀባበል እስከ ምዘና ሂደት ባሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ ማግኘት እንደቻለች ተናግራለች፡፡ ከዚህ ቀደም ተማሪዎች ለተግባር ልምምድ የሚመጡት ለምረቃ ማሟያ ብቻ ተደርጎ ይታሰብ እንደነበር የተናገረችው ሠልጣኟ አሁን ላይ ግን ሥራው ከማሟያነት ባሻገር ብቃት ያላቸው የጤና ባለሙያዎችን ከማፍራት አንጻር ያለውን ሚና ጭምር መገንዘቧን ገልጻለች፡፡

ከጂንካ ሆስፒታል የመጣው ሌላኛው ሠልጣኝ ዶ/ር የአብሥራ ንጉሴ በበኩሉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ለተግባር ልምምድ ወደ ሆስፒታላቸው እንደሚመጡና ክሂሎት ተኮር ሥልጠናዎችን እንደሚሰጧቸው ተናግሯል፡፡ ከዚህ ቀደም በተማሪዎች የተግባር ልምምድ አሰጣጥ ዙሪያ ሥልጠና ተሰጥቶ እንደማያውቅ የጠቆመው ዶ/ር የአብሥራ

በሥልጠናው ከተማሪዎች አያያዝ ጀምሮ ባሉ ጉዳዮች ላይ ጥሩ ግንዛቤ ያገኘበት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ መሰል ሥልጠናዎች በዚሁ ሥራ ላይ ለሚሳተፉ ሌሎች ባለሙያዎች ቢሰጥ የተሻለ እንደሆነም ሃሳብ ሰጥቷል፡፡

ሥልጠናው በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን በሆኑት በውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ኢየሩሳሌም በየነ እና ረ/ፕ ውብእሸት እስጥፋኖስ ተሰጥቷል፡፡ በሥልጠናው ማጠቃለያ ሠልጣኞች በቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት በማካሄድ ዕቅድ ያዘጋጁ ሲሆን የተሳትፎ ምስክር ወረቀትም ተበርክቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት