የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር ከማዕከሉ ለተወጣጡ የምርምር ባለሙያዎች ከየካቲት 30 - መጋቢት 03/2014 ዓ/ም የሚትዎሮሎጂ መረጃ ትንተናና ቪዢዋላይዜሽን (Meteorological Data Analysis & Visualization) ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ሀገራችን ያሏትን የውሃ፣ የእርሻ መሬትና የከርሰ ምድር ሀብት በአግባቡ ከመጠቀም አንፃር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚትዎሮሎጂ መረጃ ትንተናና ቪዢዋላይዜሽን መስክ ወሳኝ ሚና አለው፡፡ በመሆኑም ሠልጣኞች ሥልጠናውን በትኩረት በመከታተል ለወገን የሚጠቅም ምርምር እንዲያከናውኑ አሳስበዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ማኅበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ መምህርት ፌቨን ክንፈ ከማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መካከል የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የሚትዎሮሎጂ መረጃ ትንተናና ቪዢዋላይዜሽን ሥልጠና ባለሙያዎቹ የተለያዩ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም በግብርናና በሚትዎሮሎጂ ዘርፍ ለሚያካሂዱት ምርምር ክሂሎታቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሚትዎሮሎጂና ሃይድሮሎጂ ፋከልቲ መምህርና አሠልጣኝ ዶ/ር ቶማስ ቶሮራ በበኩላቸው ሥልጠናው የሚትዎሮሎጂ ዳታ አወሳሰድ፣ ዳታ ትንተናና ዳታ አጠቃቀምን ላይ የተሰጠ ሲሆን ለግብርና ባለሙያዎችና በግብርና ምርምር ዘርፍ ለሚሠሩ ተመራማሪዎች አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

ሌላኛው የፋከልቲው መምህርና የIUC ፕሮጀክት ተመራማሪ አቶ ያሬድ ጎድኔ አሁን ላይ ያሉት ዘመናዊ የሜትሮሎጂ መሣሪያዎች በየ15 ደቂቃው መረጃ የሚመዘግቡ መሆኑን ገልጸው መሣሪያዎቹ ያልተጠበቀ ነፋስና ዝናብ ቢፈጠር ግፊትና ፍጥነቱን ለመለየት ስለሚረዱ ተመራማሪዎች በሥራቸው፣ በአካባቢው፣ በማኅበረሰቡና በሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡

በዓለም ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሚትዎሮሎጂ ዳታ መሰብሰቢያ ማዕከላት አሉ ያሉት መ/ር ያሬድ ከማዕከላቱ የሚሰበሰቡ መረጃዎች በአንድ ማዕከል ተሰብሰበው ከአንዱ ሀገር ወደሌላ ሀገር በነጻ እንደሚተላለፉ ገልጸዋል፡፡ ይህም ከሀገር ወደ ሀገር የሚሸጋገረው አየር ምን ይዞ እንደሚመጣና ምን ሊፈጥር እንደሚችል ለመለየትና ሀገራቱ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል የመኖ ሰብሎች ተመራማሪና ሠልጣኝ አቶ ተሰማ ተስፋዬ በአስተያየታቸው ሥልጠናው ከምርምር ሥራቸው ጋር ቀጥታ ግኝኙነት ያለው እንዲሁም የግብርናውን ሴክተር ለማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው 21 የግብርና ምርምር ማዕከል ሠልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት