የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከደራሼ ወረዳ ፕላንና ልማት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በወረዳው ለሚገኙ እንዲሁም ከቡርጂና አሌ ልዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ 22 የፕላን መምሪያ እና የግብርናና ገጠር ልማት ሠራተኞች ከመጋቢት 8-10/2014 ዓ/ም ለሦስት ቀናት በGIS ሶፍትዌር ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ኃላፊ መ/ር መሐመድ ሹሬ እንደገለጹት GIS የመረጃ አያያዝን ለማዘመንና በተገቢው መንገድ ለማስቀመጥ ወሳኝና አስፈላጊ ሶፍትዌር እንደመሆኑ ሥልጠናው ክሂሎታቸውን አዳብረው የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ የሚያበቃቸው ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም በወረቀት የሚያዙ መረጃዎች እንዳይጠፉና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ እንዲሁም ለጥናትና ምርምር መነሻ የሚሆኑ መረጃዎችን ማስቀመጥ ይቻል ዘንድ ሠልጣኞች ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ለተለያዩ ልማታዊ ሥራዎች እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል፡፡

በGIS ሪሞት ሴንሲንግና GPS ላይ ሥልጠና የሰጡት የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማ/ጽ/ቤት ኃላፊና የኮሌጁ GIS ባለሙያ መ/ር ኃይለማርያም አጥናፉ እንደገለጹት GIS በመሬት አጠቃቀም ዙሪያ የግብርና ቦታን አስመልክቶ ካርታ በመሥራት አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል፡፡ እንዲሁም በGPS የተለያዩ መዳረሻ ቦታዎችን በመውሰድ ካርታዎችን መሥራት ከማስቻሉም በላይ በግብርናው ዘርፍ ወረዳው ምን ያህል የሚለማ መሬት እንዳለው የሚያሳይና ይህም ባለ ሀብቶች ወደ ወረዳው በመምጣት እንዲያለሙ የሚያስችላቸው ነው ብለዋል፡፡

ወቅቱ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምንና የተሻለ እውቀት ይዞ መገኘትን የሚጠይቅ በመሆኑ ባለሙያዎቹ በዘርፋቸው የበቁ ሊሆኑ ይገባል ያሉት የደራሼ ልዩ ወረዳ ፕላንና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ጥላሁን እንደ ወረዳ የታቀዱ እቅዶችን ለማሳካት እንዲሁም በካርታ፣ በመረጃ አያያዝ፣ በመሬት ሀብት ቆጠራና በንብረት አስተዳደር ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለመቅረፍ የሶሺዮ ኢኮኖሚክ ባለሙያዎች በተለይም ከGIS ሶፍትዌር አጠቃቀም ጋር ይበልጥ ሊተዋወቁ ይገባል ብለዋል፡፡ አቶ ሲሳይ ጥያቄያቸውን ተቀብለው ሥልጠናውን አዘጋጅተው የሰጡትን መምህራንና ዩኒቨርሲቲውን አመስግነው በቀጣይም ድጋፋችሁ አይለየን ብለዋል፡፡

ሥልጠናው በተግባር ልምምድ የተደገፈና በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ቁምነገር ያስጨበጣቸው መሆኑንና ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም ወረዳውን የሚያሳዩ የመሬት ካርታዎችን በቀላሉ መሥራትና ለተለያዩ አገልግሎቶች ማዋል እንዲችሉ የሚረዳ መሆኑን ሠልጣኞች ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት