የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በክላስተሩ የሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት ቀጠናዊ ትስስር ፎረም በዳሰሳ ጥናት የተገኙ ውጤቶች፣ የፎረሙ የ2013 ዓ/ም አፈፃፀም ክለሳና የ2014 ዓ/ም ዕቅድ ላይ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት የካቲት 26/2014 ዓ.ም በጊዶሌ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡

የኢንተርፕራይዞችን ብቃትና ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉና የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮች ማካሄድ፣ የሥልጠና፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማማከር ድጋፍ አገልግሎት መስጠትና የትምህርትና ሥልጠና ውጤታማነትን ማሳደግ፣ የትብብር ሥልጠና ፕሮግራሞችን ማጠናከር፣ ችግር ፈቺና ናሙናቸው ተፈትሾ አዋጭነታቸው የተረጋገጠላቸውን ቴክኖሎጂዎች ለአብዢ ኢንተርፕራይዞች በማሸጋገር በሚፈጠረው አቅም የኢንተርፕራይዙንና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲሁም በተቋማቱ መካከል ያለውን ቅንጅታዊ ሥራ በማጠናከር በትስስሩ ውጤታማ ለውጥና ዕድገት እንዲታይ ማስቻል የቀጠናዊ ትስስር ፎረሙ ዓላማዎች መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት የኢንደስትሪ ትስስርና ተግባር ት/ት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ሙሉጌታ ሀብቴ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት ም/ዲን አቶ ወርቅነህ ኃ/ሚካኤል እንደገለጹት በአደረጃጀቱ 75 በመቶ TVET ምሩቃን መሆን ሲገባቸው ከ75 በመቶ በላይ ከ10ኛ ክፍል በታች መሆናቸው፣ የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑ፣ ኢንተርፕራይዞች ስለ ቴክኖሎጂ መቅዳት፣ ማባዛትና መጠቀም ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑ፣ አብዛኛው ኢንተርፕራይዞች በጨረታ አለመሳተፋቸው፣ ኢንተርፕራይዙ በሚያቀርበው ምርት/አገልግሎት ተወዳዳሪነታቸው ዝቅተኛ መሆኑ በዳሰሳ ጥናቱ ከተገኙ ጉድለቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የጥራት ችግርን ለመቅረፍ የማሽን ችግር ለገጠማቸው ኢንተርፕራይዞች የብድር አቅርቦት በማመቻቸት አዳዲስ ቴክኖሎጂ ምርቶች ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የጥራት ችግርን ለመቅረፍና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የዕውቀትና የክሂሎት ክፍተት ላለባቸው ኢንተርፕራይዞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የደንበኛ እርካታን ለማሳደግ የኢንተርፕራይዙን ግንዛቤ ማሳደግ እንዲሁም ከኢንተርፕራይዝ አባላት፣ አመራሮችና ከሌሎች ማኅበራት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ መሥራት በዳሰሳ ጥናቱ የተመለከቱ የመፍትሄ ሃሳቦች መሆናቸውን አቶ ወርቅነህ ተናግረዋል፡፡

በፎረሙ የ2013 ዓ/ም አፈፃፀም ከታዩ ጠንካራ ጎኖች መካከል የቴክኒክና ሙያ አሠልጣኞችና አመራሮች የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸው፣ እስከ ኮቪድ ወረርሽን መከሰት ድረስ የተቋማት ወርሃዊ ሪፖርት መቅረቡና የቴክኖሎጂ ሥራ ሊያግዙ የሚችሉ የእሴት ሰንሰለትና የዲዛይን ሥልጠናዎች መሰጠታቸው፣ ተቋማት በፈቃደኝነት የውይይት አስተናጋጅነት መውሰድና በጥሩ ሁኔታ መሸኘት መቻላቸው፣ ተቋማት ያሉበትን ደረጃ በመገምገም የውስጥ አቅማቸውን ለመገንባት ምቹ ሁኔታ መፈጠር፣ የኢንተርፕራይዙን የድጋፍ ጥራት ችግር ለመፍታት የዳሰሳ ጥናት መጀመሩና ውይይት መደረጉ ይጠቀሳሉ፡፡

በአንፃሩ የፎረሙ ተሳታፊ ተቋማት ተቋማዊ ተልዕኮ በመያዝ የፎረሙን ተግባር መዘንጋት፣ አዳዲስ ተቋማት በፎረሙ ተገኝተው ልምድ ለመቅሰምና የጋራ ኃላፊነት ለመወጣት የዝግጁነት ማነስ፣ ፎረሙ በበጀት ተደግፎ አለመመራት፣ የፎረሙና የተቋማት ተልዕኮ መደበላለቅ፣ ውጤትን መሠረት ያደረገ የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ሥርዓት አለመከተል፣ ዕቅዶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ተፈፃሚ አለመሆን እና የመሳሰሉት ደካማ ጎኖች በመድረኩ ተነስተዋል፡፡

ጥናትና ምርምር ማካሄድ፣ የእሴት ሰንሰለት ዝግጅት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ ፍተሻና ሽግግር ማካሄድ፣ የአቅም ግንባታ ሥራ መሥራት፣ የማማከር አገልግሎት መስጠት፣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማሳደግ፣ ልምድ ልውውጥ ማካሄድ፣ አዳዲስ ተቋማትን መደገፍ፣ በዩኒቨርሲቲዎች አቅራቢያ ያሉ የቴክ/ሙ/ት/ሥ/ተቋማት ከዩኒቨርሲቲዎች በሚቀርብ ጥያቄ መሠረት የኢንተርንሺፕ ተማሪዎችን በመቀበልና አሠልጣኞችን በመመደብ ከሙያ መስመራቸውና ከቅበላ አቅማቸው ጋር በማጣጣም ተቀብለው እንዲያሠለጥኑ ማድረግ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ዓውደ ርዕይ ማካሄድ በ2014 ዓ/ም በፎረሙ ሊከናወኑ የታቀዱ ተግባራት ናቸው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት