በአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂና ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች እድሳት የተደረገላቸው የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ማደሪያ ሕንፃዎችና በግቢ ውበት የተሠሩ ሥራዎች ተጠናቀው ከመጋቢት 8/2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአገልግሎት እንዲበቁ ተደርጓል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ከአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ትግበራዎች አንዱ የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ማሳደግ ሲሆን የማደሪያ ሕንፃዎቹና የግቢ ውበት ሥራዎቹ የትግበራው አካል ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ዩኒቨርሲቲው በ2022 ዓ/ም 11ሺህ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ይኖሩታል ያሉት ዶ/ር ዳምጠው የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ቁጥር አሁን ካለበት ደረጃ በጣም ከፍ እንደሚል ታሳቢ አድርገን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል እንደተናገሩት የትምህርት ሚኒስቴር የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች በሀገራችን እጥረት ባለባቸው የትምህርት መስኮች ለቀጣይ 5 ዓመታት 5 ሺህ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አሠልጥነው እንዲያስመርቁ ዕቅድ ይዟል፡፡ ፕሮግራሞቹን እንዲያሠለጥኑ ከተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነው ያሉት ዶ/ር አብደላ በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው መጠነ ሰፊ ተግባራትን እያከናወነ የቆየ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ማደሪያ ሕንፃዎች፣ መናፈሻና መዝናኛ ቦታዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር አብደላ ገለጻ እድሳት የተከናወነላቸው 5 ብሎክ ሕንፃዎች እያንዳንዳቸው 11 ክፍሎች በድምሩ 55 ክፍሎችን የያዙ ሲሆን ከ100 በላይ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ናቸው፡፡ የማደሪያ ሕንፃዎቹ የእንግዳ ማረፊያ፣ ሻወርና ሽንት ቤቶችን እንዲሁም የምግብ ማብሰያ ክፍሎችን ያሟሉ ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ብሎክም ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ለሚመጡ ውስን የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ምቹ የሆኑ አንዳንድ ክፍሎች ተካተው ተዘጋጅተዋል፡፡ ለሕንፃዎቹ ወለል፣ ለአካባቢያቸው እድሳትና ለግቢ ውበት ሥራ አገልግሎት ላይ የዋሉት ንጣፎች በኢንስቲትዩቶቹ የተመረቱ መሆናቸውን ዶ/ር አብደላ ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ የሆነው ዕጩ ዶክተር መስፍን ረታ በቁልፍ ርክክብ ወቅት የክፍሎቹ ዝግጅት የተሻለ መሆኑን ተናግሮ ፈጣን የዋይፋይ አገልግሎት እንዲኖር አስተያየት ሰጥቷል፡፡
በክንውኑ ሂደት የላቀ አበርክቶ ለነበራቸው ሠራተኞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት