በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ በግማሽ ዓመት ውስጥ የተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኙ የምርምር ሥራዎችን አስመልክቶ መጋቢት 13/2014 ዓ/ም በኮሌጁ ግቢና በዩኒቨርሲቲው የእርሻ ምርምር ጣቢያ የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

የቆላ ስንዴ ምርት እንዲቀንስ የሚያደርጉ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ፀረ-አረም መድኃኒቶችን መለየት፣ በቆላማ አካባቢ ቶሎ መድረስ የሚችሉ የሐባብ፣ የቲማቲምና የስኳር ድንች ዝርያዎችን ከአርባ ምንጭና አካባቢዋ የአየር ሁኔታ ጋር ማላመድ፣ በዓባያና ጫሞ ሐይቆች ዙሪያ የአፈር ጨዋማነትን ለመከላከል፣ አፈሩን ለመጠበቅና ለማከም የሚያስችሉ ለሙከራ የቀረቡ የአፈር ኬሚካሎች፣ የማረቆ ፋና በርበሬን ከአካባቢው የአየር ሁኔታ ጋር ማላመድ፣ የዓሣ ምርትን ለማሻሻልና ለማብዛት በኮሌጁ በተዘጋጁ የዓሣ ገንዳዎች ላይ እየተከናወኑ ያሉ የሙከራ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም አፕል ሳይበላሽ ማቆየት የሚያስችሉ ዘዴዎች ጉብኝቱ ካተኮረባቸው የምርምር ሥራዎች መካከል ናቸው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ብርሃኑ ለማ በኮሌጁ ለምርምር የተያዘው በጀት ሥራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ፣ ተመራማሪዎች ለሙከራ ወደ መሬት ባወረዱትና እያከናወኑ ባሉት የምርምር ሥራ ላጋጠማቸው ችግር መፍትሔ ለመስጠትና በጠቃላይ በግማሽ ዓመት ውስጥ የተከናወኑና ወደ መሬት የወረዱ የምርምር ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም ጉብኝቱ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ገለጻ ኮሌጁ ከሚያከናውናቸው የተለያዩ የምርምር ሥራዎች መካከል በተለይ የቆላ ስንዴ ምርትና ምርታማነትን የሚቀንሱ ችግሮችን መለየት አስፈላጊ ነው፡፡ ምርትና ምርታማነትን የሚቀንሱ ችግሮችን ለመፍታት በዋናነት ፀረ-አረም መድኃኒቶችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው 5 የተለያዩ ፀረ-አረም ኬሚካሎች በኮሌጁ እየተተገበሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ መድኃኒቶች አንድ ጊዜ ከተረጩ እስከ ምርት መሰብሰቢያውና ለቀማው ድረስ በሰው ኃይል የሚሠራውን ሥራ በማስቀረት ረገድ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ውጤታማውን ኬሚካል በመለየት ለኅብረተሰቡ የማሸጋገር ሥራ እንደሚሠራ ዶ/ር ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር አስተባባሪ የሆኑት መምህር አግደው አበበ በኮሌጁ የምርምር ማስተባበሪያ ስር በመደበኛ በጀት የሚደገፉ 89 የምርምር ሥራዎች እንዳሉ ጠቅሰው ከነዚህም አንዱ ግራንድ ምርምር (Grand Research) መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከምርምር ሥራዎቹ 5ቱ የተጠናቀቁ ሲሆን የቀሩቱ በሂደት ላይ መሆናቸውንም መ/ር አግደው ገልጸዋል፡፡

በጉብኝቱ የኮሌጁ ካውንስል አባላት፣ በምርምር ሥራ ላይ የሚሳተፉ መምህራንና ተመራማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት