የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ ማፍለቂያ ማዕከል ለጫሞና ለአርባ ምንጭ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች በሥራ ፈጠራ አመለካከትና የሥራ ፈጠራ ክሂሎት ላይ መጋቢት 10/2014 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የሥራ ፈጠራ ማፍለቂያ ማዕከል አስተባባሪ መ/ር አበበ ዘየደ እንደገለጹት ሥልጠናው ተማሪዎቹ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እስኪደርሱ ከወዲሁ የሥራ ፈጠራ ጽንሰ ሃሳብ እንዲኖራቸውና ጥሩ የማሰላሰያ ጊዜ እንዲያገኙ የተዘጋጀ ነው፡፡ ተማሪዎቹ በትምህርት ከሚያገኙት ዕውቀት ባሻገር መሰል ሥልጠናዎችን መውሰዳቸው በሥራ ፈጠራ ዙሪያ የአስተሳሰብ አድማሳቸውን የሚያሰፋ፣ በዘልማድ የሚሠሩ ሥራዎችን በማስቀረት በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሥራ ለመሥራት የሚያግዝ፣ ሌሎች ሰዎች ባላዩት አዲስ መንገድ ማየት እንዲችሉ የሚያደርግ እንዲሁም ሥራ ፈጣሪና ተመራማሪ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን መ/ር አበበ ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንት ት/ክፍል መምህርት ትዕግስት በላይነህ በበኩላቸው ተማሪዎቹ በዚህ የክፍል ደረጃ መሠልጠናቸው ቀጣይ ለሚኖራቸው ሕይወት ከወዲሁ እንዲያቅዱና በራስ መተማመናቸው እንዲዳብር አቅም የሚፈጥርላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎቹ ካላቸው ግላዊ ባህርይ አንጻር ራሳቸውን በመፈተሽ ድክመቶቻቸውን በመቀነስና ጥንካሬያቸውን በማጎልበት ከጥገኝነት ስሜት ተላቀው ለራሳቸውም ሆነ ለሀገር ጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሠልጣኝ ተማሪዎቹ በሰጡት አስተያየት የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን በማውጣት በተማሪነት ደረጃ የሚሠሯቸውን ሥራዎች ለማጠናከርም ሆነ ተመርቀው ሲወጡ የሥራ ፈጠራ ክሂሎታቸው ከፍ እንዲል የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወደ ፊት በቀለም ትምህርት መዝለቅ ባንችል እንኳ ውስጣችን ያለውን ዕውቀት አውጥተን በመጠቀም ሥራ ፈጣሪ እንድንሆን መነሳሳትን ፈጥሮልናልም ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት