የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2014 ዓ/ም የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ጥር 27/2014 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ግምገማው ያልተፈፀሙ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮችና ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን መለየት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክ ዕቅድ ዝ/ት/ግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስፋው ደምሴ በቀረበው ሪፖርት እንደተገለጸው በ2014 የትምህርት ዘመን በቅድመ ምረቃ 28,280፣ በድኅረ-ምረቃ በ2ኛዲግሪ 2,364 እና በ3ኛ ዲግሪ 293 በአጠቃላይ 30,937 ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ መርሃ-ግብሮች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ በመጀመሪያ ዲግሪ 25 እና በ2ኛ ዲግሪ 6 በድምሩ 31 ተማሪዎች የውጭ አገር ተማሪዎች ናቸው፡፡

የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ መምህራን ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ በየጊዜው እንዲወስዱና የመማር ማስተማር ሥራም የትምህርት ጊዜ ሳይሸራረፍ በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ እንዲከናወን ድጋፍና ክትትል ተደርጓል፡፡ በመምህራን ልማት ማዕቀፍ መሠረት ለአካዳሚክ ማዕረግ እድገት ካመለከቱ መምህራን መካከል መስፈርቱን ያሟሉ አንድ መምህር የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ፣ 3 መምህራን የተባባሪ ፕሮፌሰርነት እና 17 መምህራን የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዩኒቨርሲቲነት የተለየ በመሆኑ የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ቁጥር ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ሲሆን በዚህም መሠረት በ2014 ዓ.ም እስከ 2ኛ ሩብ ዓመት የ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ቁጥር 113 እና የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ቁጥር 25 ማድረስ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም 14 የ2ኛና 5 የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ሥርዓተ ትምህርት በዝግጅት ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ምርምርን በተመለከተ 227 ነባርና አዳዲስ ምርምሮች እየተከናወኑ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 77ቱ አዳዲስ ምርምሮች ናቸው፡፡

ከአገር ውስጥ ኢንደስትሪዎችና ከውጪ አገር ተቋማት ጋር 4 የምርምር ፕሮጀክቶችም በጋራ እየተሠሩ ሲሆን 9 የምርምር ውጤቶች በአገር ውስጥና 25 የምርምር ጤቶች በዓለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ ታትመዋል፡፡ ከሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በትብብር 2 የምርምር ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በመተግበር ላይ ሲሆኑ 8 ትላልቅ የምርምር ፕሮጀክቶች (Grand Projects) ፕሮፖዛሎች ቀርበዋል፡፡ ‹‹COVID-19››ን የተመለከቱ 28 የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በነፃ የሕግ አገልግሎት (ወክሎ በመከራከር፣ በሰነድ ዝግጅትና በምክር አገልግሎት) ለ3,467 ሕፃናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች ድጋፍ ተሰጥቷል፡፡ አገልግሎቱ በአካባቢው የሚገኙ ጠበቆች ለመሰል አገልግሎት ከሚያስከፍሉት ዋጋ ጋር ሲነፃፀር 1,335,200 (አንድ ሚሊየን ሦስት መቶ ሠላሳ አምስት ሺ ሁለት መቶ) ብር ግምት ያለው ነው፡፡ በCOVID-19 ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትና ሥልጠና በማስቀጠል 315 ጎልማሶች ደረጃ-2 አጠናቀው ተመርቀዋል፡፡

በነባር ማዕከላት በደረጃ-1 የጎልማሶች ምዝገባ የተጠናቀቀ ሲሆን አዳዲስ ማዕከላትን ለመክፈት የአመቻች ቅጥር፣ የተመዘገቡ ተወዳዳሪዎችን መረጃ የመሰብሰብና መለየት ሥራ ተሠርቷል፡፡
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከሰተውን የህልውና ጦርነት አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተመራማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ለአገር መከላከያ ሠራዊት የአንድ ወር ደመወዛቸው በበጀት ዓመቱ ተቆራጭ ተደርጎ ድጋፍ እንዲደረግ ተወስኖ እየተፈጸመ ሲሆን ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ ፈቃደኛ ተሳታፊዎች የደም ልገሳ አድርገዋል፡፡

ለአገር መከላከያ ሠራዊት ተቆራጭ እየተደረገ ካለው ገንዘብ የመጀመሪያ ዙር 10 ሚሊየን ብር ተሰጥቷ፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ ወገኖች በ1 ሚሊየን ብር የምግብ እህል ድጋፍ እንዲሁም በወሎ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኙ ወገኖች 1.5 ሚልየን ብር የሚያወጡ 700 የብርድ ልብሶች፣ 240 ጥንድ አንሶላዎችና 50 ኩንታል ፉርኖ ዱቄት ድጋፍ ተደርጓል፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊትን፣ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችንና የዘማች ቤተሰቦችን ለመደገፍ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎችንና መምህራንን በማሳተፍ በተደረገው አገራዊ የድጋፍ ዘመቻም የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ ት/ቤት 70,000 (ሰባ ሺህ) ብር እና ልዩ ልዩ አልባሳት ድጋፍ አድርጓል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተናጠልና በቅንጅት ለተለያዩ ተቋማት ባለሙያዎችና አመራሮች በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች ሥልጠናዎችን የሰጠ ሲሆን የተለያዩ ሶፍትዌሮች አጠቃቀም፣ መሠረታዊ የመረጃ ትንተና፣ የበጀት ክፍፍል ቀመር ፅንሰ ሃሳብና አሠራር ሥርዓት፣ የስትራቴጂክ ዕቅድ አዘገጃጀት፣ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ፣ የሥራ-ፈጠራ፣ የቢሮ ማሽኖች ጥገና እንዲሁም የማስተማር ዘዴ ከሥልጠናዎቹ ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን በተመለከተ ዩኒቨርሲቲው በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል በተዘጋጀው ‹‹Heart Convention›› ላይ የእንሰት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂን ጨምሮ 16 የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ለዕይታ አቅርቦ በመድረኩ በተደረገው የቴክኖሎጂ ውድድር የሁለተኛነት ደረጃን በመያዝ የቴክኖሎጂው ባለቤት ተሻላሚ ሆኗል፡፡ አራት ቴክኖሎጂዎች (ኢንዳክሽን ሞተር ኮንትሮል፣ የሸንኮራ አገዳ ጁስ መጭመቂያ ማሽን፣ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን እና ‹መልቲ-ፐርፐዝ› መክተፊያ መሳሪያ) ሥራቸው አልቆ ለማሸጋገር ዝግጁ ሆነዋል፡፡

የመምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ቅጥር፣ የሕንፃዎችና መሠረተ ልማቶች ጥገና፣ የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ የተሽከርካሪዎች የኢንሹራንስ አገልግሎት ግዢ፣ የሀብት ምዝገባ፣ አቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች፣ የዲስፕሊን ክሶች ክትትል እንዲሁም የኦዲት ግኝቶች የማስተካከያ እርምጃ እና ምላሽ መስጠት በግማሽ ዓመቱ ከተከናወኑ አስተዳደራዊ ተግባራት መካከል ተጠቅሰዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን ገጽታ ከመገንባት አንፃር በክልላዊና አገራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ በማኅበራዊ ሚዲያ በፌስቡክ፣ ቴሌግራምና በዩኒቨርሲቲው ድረ-ገጽ፣ በበራሪ ወረቀት፣ ፖስተር፣ የጋዜጣ አምድና ብሮሸር በዩኒቨርሲቲውና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ወቅታዊና ተአማኒነት ያላቸው መረጃዎች፣ ማስታወቂያዎች፣ ዜናዎችና መልዕክቶች በፎቶና በቪዲዮ ተደግፈው ተደራሽ ተደርገዋል፡፡

የ2013 ዓ/ም የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ቀጥታ ስርጭት በፋና ቴሌቪዥን፣ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በመሠረተ ልማት እና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ዘጋቢ ፊልም በዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት እንዲሁም ሌሎችም ማስታወቂያዎች፣ መልዕክቶችና ዜናዎች EBCን ጨምሮ በአገራዊና የክልል ቴሌቪዥኖች በተሳከ ሁኔታ እንዲሠራጩና ተቋማዊና አገራዊና ኩነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ የተግባቦትና የማስተባበር ሥራ ተከናውኗል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ሥራ ማስጀመር፣ የምርምር ውጤቶችና የተላመዱና የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ ማሸጋገር፣ ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና አዲስ የተጀመሩት በብቃት እንዲሠሩ መደገፍ፣ የ2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች የማስተማርና የማስመረቅ አፈፃፀም ደረጃን ማሻሻል፣ የሳውላ ካምፓስ ወሰን ውስጥ ያሉ ሰዎች ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ መሥራት እንዲሁም በጦርነቱ የተጎዱ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የተፈናቀሉ ዜጎችንና የመከላከያ ሠራዊት ቤተሰቦችን መደገፍ በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በቀረበው ሪፖርት ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት