በአዲሱ የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ ምርጫ መመሪያ መሠረት በ2012 ዓ.ም የተመረጠው የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ ሁለት ዓመት የሥራ ዘመን መጠናቀቁን ተከትሎ በአዲስ አባላት ለመተካት ከታኅሣሥ 8/2014 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የዋና ሥራ አስፈፃሚ ምርጫ ሂደት ሚያዝያ 02/2014 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻና መዝጊያ ንግግሮቻቸው እንደገለጹት ሕዝብን ማገልገል ትልቅ እርካታን የሚያሰጥ ሲሆን ዩነቨርሲቲ ከአካዳምክ ዕውቀትና ዲሲፕሊን ከምንማረው በተጨማሪ ብዙ ማኅበራዊና አስተዳደራዊ ልምዶችን ቀስመን የምንወጣበት አንዱ የሕይወታችን ምዕራፍ ነው፡፡ ዶ/ር ዳምጠው ዕድሉን አግኝቶ እንደዚህ ዓይነት አገልግሎቶችን መስጠት መቻል ለወደ ፊቱ ሕይወት ከፍ ያለ ልምድ እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል፡፡

አመራርነትን መለማመድ እጅግ ጠቃሚ ነው ያሉት ዶ/ር ዳምጠው ይህ አጋጣሚ ከማኅበረሰቡ ጋርም የመገናኘትና የመተዋወቅ ዕድል ያለው በመሆኑ ከፍተኛ እርካታንም እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎች ሲያገለግሉ የቆዩትን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ኅብረት የቀድሞ ፓርላማ አባላትን አመስግነው ለአዲሱ ፓርላማ አባላትም መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆናቸው ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አየልኝ ጎታ የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ ምርጫ በየሁለት ዓመቱ የሚከናውን ተግባር እንደሆነ ገልጸው ምርጫው ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ የሴክሽን ምርጫ መመሪያ ከላከ በኋላ ለ2ኛ ጊዜ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡ ከየሴክሽን 2.75 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያለቸው፣ በዲሲፕሊን ያልተከሰሱ፣ የሃይማኖትና የብሔር ወገንተኝነት የማይታይባቸው ተማሪዎች በዕጩነት እንደሚቀርቡ የተናገሩት አቶ አየልኝ በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱም አብላጫ ድምፅ ያገኙ አንድ ወንድና አንድ ሴት ተማሪዎች የፓርላማው የሴክሽን ተወካዮች ሆነው ይቀላቀላሉ ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የ5ኛ ዓመት ሶፍትዌር ኢንጂነርንግ ተማሪና የ2014 ዓ.ም የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ ምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተማሪ አንሙት ጎዴ ስለምርጫው ሂደት ሲናገር ከሴክሽን ተወካዮች ጀምሮ የዋናው ሥራ አስፈጻሚና የኦዲቴሮች ምርጫ ሂደት ድረስ መመሪያውን ተከትለን አስፈጽመናል ብሏል፡፡ ለዋና ሥራ አስፈጻሚነት ከ6ቱም ካምፓሶች 113 ተወዳዳሪ ታማሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን 68ቱ ለጽሑፍ ፈተና መቅረባቸውን የኮሚቴው ሰብሳቢ ገልጿል፡፡

እንደ ተማሪ አንሙት ከ68ቱ ውስጥ 16ቱ ለቃል ፈተና የቀረቡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በብሔርና በጾታ አስተዋጽኦ የአፈጻጸም መመሪያ መሠረት 8ቱ ለዋና ሥራ አስፈጻሚነት ውድድር የስትራቴጂክ ትግበራ ዕቅድ ለፓርላማው እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡ ይህንን ተከትሎ በተካሄደው የድምፅ አሠጣጥ ሥነ-ሥርዓት ተማሪ ደስአለው ቆለጭ ፕሬዝደንት፣ ተማሪ ምህረት ተካልኝ ም/ፕሬዝደንትና ተማሪ ናርዶስ ደምሰው ሆነው መመረጣቸውን ሰባሳቢው ተናግሯል፡፡

ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ምርጫ በኋላም በተካሄደው የኦዲተሮች ምርጫ ተማሪ ተመስገን አዲሱ ዋና ኦዲተር፣ ተማሪ ሣምራዊት ትግስቱ ም/ኦዲተርና ተማሪ ፍሬሕይወት ስሜ ኦዲተር ሆነው መመረጣቸውን እንዲሁም በቀጣይም የአፈ-ጉባዔ ምርጫ እንደሚካሄድ የአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢው ተማሪ አንሙት ገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሪካል ኢንጂነርንግ የ4ኛ ዓመት ተማሪና አዲሱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፕሬዝደንት ተማሪ ደስአለው ቆለጭ በምርጫው የተሰማውን ደስታ ሲገልጽ ምርጫው ከመጀመሪያው እስከ ፍጻሜው የነበረው ሂደት በአዲሱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ፓርላማ ምርጫ መመሪያ መሠረት የተፈጸመ በመሆኑ ደስ የሚል ነበር ብሏል፡፡

የፓርላማው አባላት ዓላማዬን ተረድተው እንዳገለግላቸው ዕድል ስለሰጡኝ እጅግ በጣም አስደስቶኛልም ሲል ተማሪ ደስአለው ተናግሯል፡፡ በውድድሩ ሂደት ለፓርላማው የገባሁትን ቃል ወደ መሬት አውርጄ ለመሥራት ዝግጁ ነኝ ያለው ተመራጭ ፕሬዝደንት ደስአለው ለስኬታማነቱ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ከጎኑ እንዲሆኑና እንዲደግፉት ጠይቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሶፍትዌር ምኅንድስና የ4ኛ ዓመት ተማሪ ምህረት ተካልኝ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረት አዲሷ ተመራጭ ም/ፕሬዝደንት ስትሆን ስለምርጫው በሰጠችው አስተያየት ምርጫውን እንደማሸንፍ ጠብቄ ነበር ነገር ግን ባገኘሁት ዕድል ተማሪውን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፤ ግዴታዬንም ለመፈጸም ቃል እገባለሁ ብላለች፡፡

የ5ኛ ዓመት የኤሌክትሪካል ምኅንድስና ተማሪ ኦሮባ ዲነግዴ በበኩሉ ለ3ኛ ጊዜ የፓርላማ አባል ሆኖ መመረጡን በማስታወስ ሁሉም ተወዳዳሪዎች ለምርጫ ውድድር ሲሉ የምናገሩትንና የሚገቡትን ቃል ከተመረጡ በኋላ ሲተገብሩ አይታይም ያለ ሲሆን ስለሆነም ፓርላማው ድምጹን ሰጥቶ የመረጣችሁ ተማሪዎች በተሰጣችሁ ኃላፊነት በተናገራችሁትና በገባችሁት ቃል መሠረት እንድታገለግሉን እጠይቃለሁ፤ በምርጫው የተሳካላችሁ ተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ፤ የሥራ ዘመናችሁም የሠላምና የስኬት እንዲሆን ከወዲሁ እመኛለሁ ብሏል፡፡

የምርጫው ሂደት አፓረንትሽፕ በወጡ ፋከልቲዎች ምርጫ በጊዜ ባለመጠናቀቁ፣ በፈተና እና ሌሎች መሰል ምክንያቶች ረዘም ያለ ጊዜ ቢወስድም በሠላማዊና ዴምክራሲያዊ ሁኔታ መጠናቀቁ ስኬት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በፕሮግራሙ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛንና የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንትና የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅንን ጨምሮ የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከልና የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሮችና አመራሮች እንዲሁም የአዲሱ የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ አባላት ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት