የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል በሥራ ፈጠራ አመለካከትና በመሠረታዊ የሥራ ፈጠራ ክሂሎት ዙሪያ ሚያዝያ 29/2014 ዓ/ም የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ለዓባያ፣ ጫሞ፣ ኩልፎ፣ ነጭ ሳርና ዋናው ግቢ ተመራቂ ተማሪዎች ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥራ ፈጠራ ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ ሥልጠናው ለተመራቂ ተማሪዎች በሥራ ፈጠራ ክሂሎት ላይ በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ ተመራቂዎች የተለያዩ አማራጮችን ተመልክተው ራሳቸውንና ሌሎችን መጥቀም የሚያስችል አቅም ይፈጥርላቸዋል ብለዋል፡፡

ራስን ማወቅ ለሥራ ፈጠራ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ያሉት አሠልጣኝ መ/ርት አስቴር ሰይፉ ሥልጠናው ተማሪዎቹ ለሥራ ፈጠራ፣ ለራሳቸው እና ለሌላው ሰው ያላቸው አመለካከት መልካም አንዲሆን በማድረግ ተቀጣሪ ሳይሆኑ ቀጣሪ በመሆን ለቀጣይ ትውልድ የሥራ ፈጠራ እድልን እንዲያመቻቹ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሠልጣኝ መ/ር አሰግድ አጥናፉ በበኩላቸው ሠልጣኞች የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ፣ እችላለሁ የሚለውን ስሜት አዳብረው በመነቃቃት ወደ ሥራ እንዲገቡና ውጤታማ እንዲሆኑ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ የጊዜና የሀብት አጠቃቀም፣ የዕቅድ አዘገጃጀትና ተያያዥ ጉዳዮች  ላይ ግንዛቤን በመፍጠር ተማሪዎቹ ዕውቀት እንዲጨብጡ መደረጉን አሠልጣኙ አብራርተዋል፡፡

ሠልጣኝ ተማሪዎች ከሥልጠናው ያገኘነው ዕውቀት ለቀጣይ ሥራችን አጋዥና ለሥራ በር የሚከፍትልን በመሆኑ ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረ እንዲሁም ሥራ በመፈለግ ጊዜያችንን ከማጥፋት የሚታደገን ነው ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት