የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በደቡብ ክልል ከሚገኙ የተለያዩ ሆስፒታሎች ለተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች፣ የኦፕሬሽን ክፍል ነርሶች፣ አንስቴዥያ ባለሙያዎችና የሕክምና ዶክተሮች ከግንቦት 19-21/2014 ዓ/ም ‹‹ሰላማዊ የኦፕሬሽን ክፍልና የተሻለ የማገገም ሂደት/Safe Operating Room (OR) and Enhanced Recovery after Surgery Training›› በሚል ርዕስ ሀገር አቀፍ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በመክፈቻ ንግግራቸው በጤናው ዘርፍ የተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ገልጸው ሥልጠናውም በኦኘሬሽን ክፍል ውስጥ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻልና ደኅንነቱ የተጠበቀ የኦኘሬሽን ሥርዓት እንዲካሄድ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ሥልጠናው ኦፕሬሽን ሲሠራም ሆነ ከተሠራ በኋላ አደጋን ከመቀነስ አኳያ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የባለሙያዎችን አቅም የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ደኅንነቱ የተጠበቀ ኦኘሬሽን ማካሄድና በኦኘሬሽን ክፍል አካባቢ በባለሙያዎች የሚከሰቱ ችግሮችን ማስቀረት ዋነኛ ግባቸው መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ደስታ ሁሉም የጤና ባለሙያዎች በየደረጃቸው በኃላፊነት፣ በመተባበርና በመደጋገፍ ሊሠሩ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎት ጥራት ዳይሬክቶሬት ም/ዳይሬክተር ዶ/ር ደሳለኝ በቀለ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለ5 ዓመት ያወጣውን ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት አድርጎ ባለሙያዎች ልምዳቸውን እንዲካፈሉና እርስ በእርስ እንዲማማሩ እንደሚደረግ ገልጸው በቀዶ ሕክምና ላይ ጥራትና ቅልጥፍናን ለማሻሻል ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ም/ዳይሬክተሩ የሥልጠናው ዓላማ የሕክምና ጥራትንና ደኅንነትን ማሻሻል በመሆኑ ባለሙያዎቹ ከሥልጠናው በኋላ ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች ማጋራትና ለማኅበረሰቡ ተገቢውን አግልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተርና በሙያቸው የነርቭና ቀዶ ጥገና ስፔሺያሊስትና አሠልጣኝ ዶ/ር አንዱዓለም ደነቀ ሁለት ዐበይት ጉዳዮች በሥልጠናው መዳሰሳቸውን ተናግረው አንዱ ደኅንነቱ የተጠበቀ ኦፕሬሽን አደራረግና ህመምተኞች ከኦኘሬሽን በኋላ ቶሎ ወደ ተሻለ የጤና ሁኔታ የሚመለሱበት መንገድ ሲሆን ሌላኛው የጥሩ ቡድን ምንነት፣ አመራርና የሚያስፈልጉ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል፡፡ በኦኘሬሽን ወቅት የጽዳት፣ የመላላክና የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ሠራተኞች የራሳቸው ሚና ስላላቸው ከቡድኑ ጋር ተቀናጅተው የሚሠሩበት መንገድ እና ከኦፕሬሽን በፊትና በኋላ ለታካሚ የሚደረግ ክትትልን አስመልክቶ ሥልጠናው አቅም የሚፈጥርና ደኅንነቱ የተጠበቀ ኦኘሬሽን እንዲያከናውኑ የሚረዳ መሆኑን ዶ/ር አንዱዓለም ተናግረዋል፡፡

በጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪምና የኦፕሬሽን ክፍል ኬዝ ቲም መሪ የሆኑት ሠልጣኝ ዶ/ር ዳግማዊ አወቀ ከሥልጠናው ከተለመደው አሠራር ይልቅ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በቡድን በተሻለ ሁኔታ ለመሥራት የሚያስችል ግንዛቤ አግኝተንበታል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት