የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ለሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ ለቴክኖሎጂና ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ከግንቦት 19-20/2014 ዓ/ም አቀባበልና የላቀ ውጤት ላመጡ ነባር ሴት ተማሪዎች የሽልማት መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ሴቶችን መደገፍና ማበረታት ሀገርን የማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ሴት ተማሪዎች የሚገጥሟቸውን የአቻ ግፊቶች በመቋቋምና የሚሰጡ የድጋፍ ትምህርቶችን በመከታተል ለጥሩ ውጤት መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የቴክኖሎጂና ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቡድን መሪ ወ/ሪት አዳነች እልፍነህ መርሃ ግብሩ አዲስ ለሚገቡ ሴት ተማሪዎች የሥራ ክፍሉን ተግባራት ለማስተዋወቅና የሚገጥሟቸውን ችግሮች እንዴት ማለፍ እንደሚገባቸው መረጃ ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሥርዓ ጾታ ጉዳይ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚመለከት መሆኑን በመገንዘብ ለሴቶች እኩልነት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ወንዶች አጋር በመሆን ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸውና ሴቶችም የመጡበትን ዓላማ ጠንክረው በማሳካት አይችሉም የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ማስወገድ እንደሚጠበቅባቸው ቡድን መሪዋ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ሴቶች ካለባቸው የሥራ ጫና አንፃር ካሰቡበት እንዲደርሱ የሁሉንም ድጋፍና ትኩረት እንደሚሻ ተናግረው ምንም እንኳ የማይመቹ ሁኔታዎች ቢኖሩም ሴት ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት ጠንክረው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡ ሴት ተማሪዎችን ለማበረታታት የመግቢያ ውጤት ሴቶችን የሚደግፍ በመሆኑ በኮሌጃቸው የሴቶች ቁጥር ከወንዶች ይልቅ ከፍ እንዲል ማድረጉን ዶ/ር ታምሩ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ ሴት መምህራንና ተሸላሚ ተማሪዎች የጊዜ አጠቃቀም፣ የአጠናን ስልቶች፣ ሊኖሩ የሚገቡ ግለ ባህርያትና መሰል ጉዳዮች ላይ የሕይወት ልምድና ተሞክሮዎቻቸውን አካፍለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት