የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ለ2014 ዓ/ም አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ከግንቦት 13-21/2014 ዓ/ም የሕይወት ክሂሎት ሥልጠና ሰጥቷል::ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ አብዛኛዎቹ ሴት ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ርቀው ሲመጡ የመጀመሪያቸው እንደመሆኑ ትምህርታቸውን በአግባቡ የመከታተል ብሎም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ሁሉ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ የሥልጠናው ዓላማ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በብቃት በመወጣት ስኬታማ የሚሆኑበትን ክሂሎት ማስጨበጥ መሆኑንም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተለይም ተማሪዎቹ በራስ መተማመናቸውን የሚያዳብርላቸውና የአቻ ግፊትን በቀላሉ መቋቋም የሚያስችላቸው በመሆኑ ግባቸውን ለማሳካት ሩቅ ዓልመው እንዲሠሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና ት/ክፍል መምህርና አሠልጣኝ አቶ ዘለቀ ገብሩ እንደተናገሩት በተለያዩ ጊዜያት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተደረጉ ጥናቶች የስነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮች በከፍተኛ ሁኔታ በሴቶች ላይ እንደሚስተዋሉ ያሳያሉ፡፡ ተማሪዎች ዓላማቸውን በማሳካት ሂደት ውስጥ ከሚገጥሟቸው እንቅፋቶች መካከል ከስነ-ተዋልዶ ጤና ጋር የተያያዙ ችግሮች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው አሠልጣኙ ገልጸዋል፡፡ የችግሩ ስፋት ስር የሰደደ በመሆኑ ተማሪዎች ግንዛቤው ኖሯቸው ከወዲሁ ራሳቸውን እንዲከላከሉ ለማስቻል ሥልጠናው መዘጋጀቱንም አሠልጣኙ ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ የሳይኮሎጂ መምህር፣ የካምፓሱ የምርምር አስተባባሪና አሠልጣኝ አቶ ዘርይሁን አያሌው በበኩላቸው አዲስ ገቢ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመጡ አዲስ የሚሆንባቸውን አካባቢ እንዴት መዋሐድ እንዳለባቸው ግንዛቤ በመስጠት ሴት ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና ውጤታማ እንዲሆኑ እንዲሁም የተሻሉ ተሞክሮዎችን በመውሰድ በትምህርታቸው እንዲተጉ ሥልጠናው ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በራስ መተማመን፣ የአጠናን ዘዴ፣ የአቻ ግፊትን መቋቋም፣ የስነ-ተዋልዶ ጤና፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የፈተና አወሳሰድ፣ የግጭት አፈታት፣ የውሳኔ አሰጣጥ፣ ጭንቀትን መቋቋም፣ ጾታ ተኮር ጥቃትን መከላከል እና የመደራደር ክሂሎት ሥልጠናው ካተኮረባቸው ነጥቦች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ሠልጣኝ ተማሪዎች በአስተያየታቸው ሥልጠናው ለአካባቢው እንግዳ ቢሆኑም አካባቢውን በቀላሉ ለመልመድ እንደጠቀማቸው ተናግረዋል፡፡ በግቢ ቆይታቸው ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ ተግዳሮቶችና ሊደርስባቸው ከሚችል ጉዳት እንዴት ራሳቸውን እንደሚከላከሉም ግንዛቤ እንዳገኙበት ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት