የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት/AWTI/ ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት/EWTI/ ጋር በመተባበር ለኢንስቲትዩቱ መምህራን፣ ተመራማሪዎችና ተማሪዎች በውሃ ንጽሕና አጠባበቅና በፍሳሽ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከግንቦት 19-21/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመክፈቻ ንግግራቸው ‹‹WASH Alliance International/ዋሽ አሊያንስ ኢንተርናሽናል›› ድረ-ገጽን ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት በአሁኑ ጊዜ 2.1 ቢሊየን ሰዎች ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የማያገኙ ሲሆን 4.5 ቢሊየን ሰዎች ደግሞ ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽሕና አገልግሎት እያገኙ አይደለም፡፡
በኢትዮጵያ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን ለሁሉም ዜጎች ለማዳረስ ጥረት ቢደረግም በርካቶች ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት እየተቸገሩና በውሃ ወለድ በሽታዎች እየሞቱ ነው ያሉት ዶ/ር ዓለማየሁ የመስኩን ባለሙያዎች አቅም ለማጎልበት መሰል የአቅም ግንባታ ሥልጠና በተለይ በምርምርና በዕውቀት ሽግግር ላይ የላቀ ሚና እንደሚኖረው በመግለጽ ሥልጠናውን ላዘጋጁ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመጠጥ ውሃ ቡድን መሪ አቶ ወንድማገኝ አድማሱ ተቋማቸው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በውሃ ምኅንድስና ዘርፍ በምርምርና ተማሪዎችን አፓረንት/Apprenticeship/ በመላክ ዙሪያ አብሮ ለመሥራት ከ5 ዓመታት በፊት የተፈራረመውን የሁለትዮሽ ስምምነት/MoU/ በቅርቡ በድጋሚ እናድሳለን ብለዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የመጠጥ ውሃ ምኅንድስና ቡድን መሪና አሠልጣኝ አቶ ለሜሳ ፈያዳ በበኩላቸው በሀገራችን የግንባታ ፕሮጀክቶች ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ክትትል እንደማይደረግ የጠቀሱ ሲሆን ፕሮጀክቶች ዘላቂ አገልግሎት መስጠት በሚችሉበት ሁኔታ፣ ማኅበረሰቡ የውሃ ንጽሕና አያያዝና የፈሳሽ አወጋገድ ግንዛቤ እንዲኖረው በማስቻል ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሰጥ ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ደመላሽ ወንድማገኘው እንደገለጹት ሥልጠናው በኢንስቲትዩቱ 4ቱም ፋከልቲዎች ለሚያስተምሩ መምህራንና ተማሪዎች የሚሰጥ ሲሆን በተለይ የውሃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና መምህራንና ተማሪዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ዓላማውም በሀገራችን በውሃ ምኅንድስና ዘርፍ የሚሠሩ የዲዛይን፣ የኮንስትራክሽን ጥገና፣ የውሃ ቁጥጥርና ንጽሕና አጠባበቅ እና የውሃ አቅርቦት ባለሙያዎች፣ መምህራንና ተመራማሪዎችን ዕውቀት ከፍ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተ/ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ገለታ ጥላሁን የውሃ፣ ንጽሕና አጠባበቅና የፍሳሽ አገልግሎት በኢትዮጵያ ትኩረት ያልተሰጠውና ብዙ ሊሠራበት የሚገባ መስክ ሲሆን ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲዎች ለዘርፉ ተመራቂ ተማሪዎች ተመርቀው ከመውጣታቸው በፊት እንዲሁም ለመምህራንና ተመራማሪዎች ክሂሎታቸውን እንዲያሻሽል እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ5ኛ ዓመት የውሃ አቅርቦትና የአካባቢ ምኅንድስና ተማሪና የሥልጠናው ተሳታፊ ተማሪ ሰኢድ ይማም ሥልጠናው ከዩኒቨርሲቲ ተመርቄ ስወጣ በዘርፉ ብዙ እንድሠራ መንገድ አሳይቶኛል ብሏል፡፡

‹‹WASH Alliance International›› በ ‹‹WASH/Water Sanitation and Hygiene›› ማለትም በውሃ ንጽሕና አጠባበቅና በፍሳሽ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት በማድረግ መገልገያዎችንና ልምዶችን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት እና የዘርፉን አስተዳደራዊ ሁኔታዎች ለማሻሻል በታዳጊ ሀገራት ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት