በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ በሎጅስቲክ እና ሰፕላይ ቼይን ማኔጅመንት ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ አቶ ሀቢብ ሳኖ “International Virtual Conference on Intelligent Computing in Humanity, Agriculture, Science & Technology” በሚል ርዕስ በተካሄደ ቨርቹዋል ኮንፈረንስ ላይ ቁልፍ ንግግር አቅርበዋል፡፡

አቶ ሀቢብ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሱ ሕንድ ሀገር ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር የተዘጋጀ ሲሆን የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ቁልፍ ንግግር እያዘጋጁ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

መምህራን፣ ተመራማሪዎችና ተማሪዎች በመሰል ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መገናኘታቸው እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ሀገር ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ መምህራንና ተመራማሪዎች ከመማር ማስተማር፣ ከምርምርና ከማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎቻቸው ጎን ለጎን መሰል እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሳተፉ አቶ ሀቢብ አሳስበዋል፡፡  

ቁልፍ ንግግሩ የሎጅስቲክና ሰፕላይ ማኔጅመንት ምንነት፣ በተላይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ያለው ፋይዳ፣ ዘርፉ በአግባቡ ያልተጠና እንደመሆኑ ለተመራማሪዎች የጥናትና ምርምሮች አስፈላጊነት ጥቆማ እንዲሁም የኢንደስትሪዎች የዘርፉን ዕውቀት የመጠቀም አስፈላጊነትና የገበያ ተወዳዳሪነት የመሳሰሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

በኮንፍረንሱ ላይ የተለያዩ ቁልፍ ንግግሮች የቀረቡ ሲሆን የዓለማችን ታዋቂ የኢንደስትሪ ባለቤቶች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የመንግሥት አካላት፣ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ የውጪ ሀገር ዜጋ መምህራን እንዲሁም በሳውላ ካምፓስ የሎጅስቲክ እና ሰፕላይ ቼይን ማኔጅመንት ት/ክፍል መምህራንና ተማሪዎች፣ የትምህርትና የሥራ ክፍል ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት