አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሰገንና ጨልኮ ወንዞች ላይ የመስኖ ውሃ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶች ዲዛይንና ጥናት ለማካሄድ ከደቡብ ዲዛይን፣ ግንባታና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር ግንቦት 26/2014 ዓ/ም ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ የሰገን ወንዝ በኮንሶ ዞንና በቡርጂ ልዩ ወረዳ መካከል ሲሆን የጨልኮ ወንዝ ደግሞ በመሎ ኮዛ ወረዳ በቦረዳ ጋዘር የሚገኙ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች በመሰል የዲዛይንና ጥናት ሥራዎች መሳተፋቸው የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅና የሙያ አቅምና ክሂሎታቸውን ከማዳበር ባለፈ ለሀገር ልማትና ለማኅበረሰቡ ሕይወት መለወጥ የጎላ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ፕሬዝደንቱ በዲዛይንና ጥናት ሥራው የሚሳተፉ የዩኒቨርሲቲው መምህራን በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው በመሆኑ ውጤታማ ሥራ የመሥራት አቅም ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል የውል ስምምነቱ በሁለቱ ወንዞች ላይ የመስኖ ውሃ ግድብ ዲዛይንና ጥናት ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ በሰገን ፕሮጀክት 8 ሺህ ሄክታርና በቦረዳ ጋዘር ፕሮጀክት እስከ 1 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ውሃ ማልማት እንደሚያስችሉ ገልጸዋል፡፡ የዲዛይንና የጥናት ሥራው ግድቦቹ በቂ ውሃ መያዝ የሚችሉበትን እንዲሁም ዝናብ በማይኖርበትና በበጋ ወራት በተጠራቀመው የግድብ መስኖ ውሃ በማልማት በዓመት 3 ጊዜ ያህል ማምረት የሚያስችል ሁኔታን እንደሚያካትት ዶ/ር አብደላ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ዲዛይን፣ ግንባታና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ውባየሁ ትዕዛዙ ተቋማቸው የመስኖ፣ መንገድ፣ ሕንጻ፣ ድልድይና ሌሎች ተያያዥ ግንባታዎች ጥናት፣ ዲዛይን፣ ቁጥጥርና የማማከር ሥራዎችን እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ ተቋማቸው በዘርፉ የረጅም ዓመታት ልምድ ያለው ሲሆን ከዚህ ቀደም በደቡብ ክልል ብቻ አገልግሎት እየሰጠ መቆየቱን ጠቅሰው በአሁን ሰዓት አዲስ የተቋቋሙ የሲዳማና የደቡብ ምዕራብ ክልሎችን ጨምሮ በ3ቱም ክልሎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ከቤኒሻንጉል ክልል፣ ከአዲስ አበባ መስተዳድርና ከአፋር ክልል ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከደቡብ ዲዛይን፣ ግንባታና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በርካታ የፕሮጀክት ሥራዎችን መሥራቱ የተጠቀሰ ሲሆን የፕሮጀክቶቹ ወጪ የሰገኑ 7 ሚሊየን እና የጨልኮ 2.9 ሚሊየን በአጠቃላይ እስከ 10 ሚሊየን ብር ሙሉ በሙሉ በክልሉ የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት