የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት ከሃንስ ሰይደል ፋውንዴሽን/Hanns Seidel Foundation/ እና ከሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር የምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት (United Nations Human Rights Office of the High Commissioner, East African Branch) ጋር በመተባበር ‹‹አስገዳጅ ስደትና ፆታዊ ጉዳዮች በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ እይታ›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ የመጀመሪያው ዓለም ዓቀፋዊ የምርምር አውደ ጥናት ከሰኔ 1-2/2014 ዓ/ም ድረስ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ስደት በአብዛኛው በታዳጊ ሀገሮች እየተከሰተ የሚገኝ ክስተት ሲሆን ይህም ለሰው ልጆች ደኅንነት እጅግ አደገኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማረ ሰው ኃይልን ከማፍራት ባሻገር በሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየትና የመፍትሄ ሃሳብ ማምጣት፣ ዜጎችን ማሠልጠንና የመሳሰሉ ሥራዎችን የሚያከናውኑ በመሆኑ ከሰብዓዊ መብት፣ ከስደትና ፆታዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚሠሩ ተግባራት ትኩረት ሊሰጣቸውና በጥናትና ምርምር የተደገፉ የመፍትሄ ሃሳቦች ሊሰጡ ይገባል ብለዋል፡፡ ከዚህ አንጻርም ዩኒቨርሲቲው እንደ ዕውቀትና ምርምር ተቋምነቱ እንዲሁም እንደ ማኅበረሰብ አገልግሎት ሰጪነቱ የሀገርና የውጪ ሀገር ተፈናቃዮችንና ስደተኞችን ለመርዳት የሚያስችሉ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች በማካሄድ ላይ የሚገኝ መሆኑንና ይህም በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

ስደተኝነት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ፆታዊ ጉዳዮች ተያያዥ መሆናቸውን መገንዘብ እንደ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ጭምር በጣም አስፈላጊና ወቅታዊ ጉዳይ ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተባባሪ ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች የስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ ይህም በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ሌሎች በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ በሆኑ ችግሮች በሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ወይም የአንድን ሀገር ድንበር አቋርጦ በማለፍ እንቅስቃሴ ምክንያት የሚሆን ነው፡፡

እንደ ተ/ፕ በኃይሉ ችግሩም በሀገር ኢኮኖሚ፣ ገጽታ ግንባታና ፖለቲካ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ያለው መሆኑን በመግለጽ ስደትን እና የእርስ በርስ ግጭትን ለማስወገድ፣ ሠላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚያስችሉና በጉዳዩ ላይ ትኩረት ያደረጉ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የተሠሩ የምርምር ውጤቶችንና የተሻሉ ልምዶችን መሠረት በማድረግ መሰል ውይይቶችን ማካሄድ መፍትሄ ለመፈለግ በጣም ወሳኝ ይሆናል ብለዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት ዲን መ/ር እንየው ደረሰ እንደገለጹት በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገራት አንጻር ከፍተኛ ተፈናቃይ ያለባት ሀገር እንደመሆኗ በኢትዮጵያ ያለውን የሕግ ማዕቀፍ፣ የሕግ ሽፋኑ ተደራሽነትና ለተፈናቃዮች የሚደረግ የጥበቃ ሁኔታ እንዲሁም እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሄ እርምጃዎች አስመልክቶ የኢትዮጵያን ሕግ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር በማገናኘት እየተሰጣቸው ካለው ትኩረት አንጻር በሌሎች አካባቢዎች፣ ሀገራትና ዓለማት የተሠሩ ምርምሮችን በማምጣት ልምዶችንንና መፍትሄዎችን መካፈል ነው፡፡ በተጨማሪም ዲኑ መንግሥት ዜጎችን ከተለያዩ ጥቃቶች የመጠበቅ፣ ጥቃትም ከደረሰ በኋላ ዜጎች ወደ ቦታቸውና የቀድሞ ሕይወታቸው እንዲመለሱ አስቻይና በምርምር የተደገፉ መንገዶችን ከሌሎች ተሞክሮዎች በመለዋወጥ ግንዛቤን ማሳደግ ነው ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር የምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሰብዓዊ መብት ባለሙያ አቶ ምስክር ጌታሁን ባቀረቡት ቁልፍ ንግግር ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ያጋጠማትን የሀገር ውስጥ የተፈናቃዮች ችግር ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቁ ጉዳዮች ተዳስሰዋል፡፡

አቶ ምስክር በአሁኑ ሰዓት በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በማኅበረሰብ እና በተለያዩ ቡድኖች መካከል በዘር፣ በሐይማኖት እና በመሬት ግጭት ምክንያት በሚከሰቱ ጦርነቶች እንዲሁም መንግሥት ሕግን ለማስከበር በሚወስዳቸው የጦር እርምጃዎች ከቀዬኣቸው ለደኅንነታቸው ሲሉ የተሰደዱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በተባበሩት መንግሥታት ስታስቲክሶችና የተለያዩ የመንግሥት ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ወደ 5.1 ሚሊየን መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ ከሚደርሱ ጉዳቶችም መካከል ለአብነት የሕይወት ማጣትና የአካል ጉድለት፣ ፆታዊ ጥቃቶች፣ ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፡- ከቤተሰብ፣ ከትምህርት፣ ከጤና እና ከሌሎች መሠረተ ልማቶች መነጠል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የሰብዓዊ መብት ባለሙያው አክለውም በእነዚህ ምክንያቶች ላይ መረጃ በማጠናቀር የመብት ባለቤቶች መብታቸውን እንዲያውቁ፣ የግዴታ ኃላፊነት የሚጣልባቸው መንግሥት እንዲሁም ሌሎች ተቋማት ደግሞ ከግዴታ በሚመነጭ ኃላፊነትን እንዲወጡ ለማስቻል እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሌሎች በአካዳሚክ ዙሪያ ያሉ ተቋማትና አውደ ጥናቱን የታደሙ ባለድርሻ አካላት በበለጠ ሁኔታ ምርምር በመሥራት ፍትህ እንዲዳረስ፣ የመንግሥት አካላትም ተጠያቂነትን ማስረጽ ላይ ትኩረት እንዲሰጡ እንዲሁም ተገቢውን ክትትል ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በየአቅራቢያችን ግጭቶች በተደጋጋሚ እንዳይከሰቱ የሀገር ሽማግሌዎችንና የሐይማኖት መሪዎችን በማሳተፍ እንዲሁም ኅብረተሰቡን በሙሉ ያሳተፈ የእርቅ ስምምነት፣ የፍትህ ሥራ በመሥራት ተፈናቃዮችን ቀድሞ ወደ ነበረ ሕይወታቸው መመለስና ድጋፍ ለሚፈልጉት ድጋፍ የማድረስ ሥራን ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሠሩ አቶ ምስክር አደራ ብለዋል፡፡ ኮምሽነር መሥሪያ ቤቱም ከጎናቸው መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መ/ር እና ተመራማሪ ዶ/ር ታገሰ አቦ ‹‹ከስደት ተመላሾችን በኢኮኖሚ መልሶ ማቋቋም ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትና የሚሠሯቸውን ሥራዎች ልየታ›› ላይ ያተኮረ ጥናት አቅርበዋል፡፡ በዚህም ባለድርሻ አካላት ያላቸው አቅም፣ ተግዳሮቶችና ምርጥ ተሞክሮዎች የመለየት ሥራ መከናወኑን ዶ/ር ታገሰ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ከስደት ተመላሽ ለሆኑት ለችግሮቻቸው መፍትሄ የሚያገኙበትን አድራሻና መንገድ በማሳየት በቀላሉ በኢኮኖሚ መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚቻል በጥናታቸው ጠቁመዋዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ በአስገዳጅ ስደት፣ በሴቶች መብትና ከሳውድ አረቢያ ተመላሽ ዜጎች እጣ ፈንታና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሁለት ቁልፍ ንግግሮችና 6 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ከኬንያ፣ ከኦክስፎርድ ብሩክስ ዩኒቨርሲቲ፣ ከህንድና ሀገር ውስጥ ካሉ የሕግ ት/ቤቶች፣ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮምሽነር እና ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት የመጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ በፕሮግራሙ መጨረሻም ለመርሃ-ግብሩ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ እንግዶችና መ/ራን የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት