የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ከሃንስ ሰይደል ፋውንዴሽን/ Hanns Seidel Foundation/ ጋር በትብብር ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ላይ ለመሳተፍ ከመጡ የተለያዩ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ተቋማት ጋር በሕግ፣ ፍትህ፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ በስደት ዙሪያ በትብብር መሥራት በሚቻልበቻው አማራጮች ላይ ግንቦት 30/2014 ዓ/ም በኃይሌ ሪዞርት ውይይት ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ አገ/ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንደ ሀገር ከተለዩ 8 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ እንደመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በተፈጥሮ ሀብት፣ ግብርና፣ ጤና፣ በትምህርት፣ በማዕድን ልማት፣ በቱሪዝም፣ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን፣ በሰብዓዊ መብቶችና አስተዳደር እና ሌሎች መስኮች የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ከተባባሪ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ ነው፡፡ ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለብቻው መወጣት ከሥራው ውስብስብነትና ስፋት አንጻር አዳጋች በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ካሉ መንግሥታዊና ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመደጋገፍ ለመሥራት ምን ጊዜም ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ በትብብር ከሠራን የጋራ ዓለማችንን በቀላሉ ማሳካት ስለሚቻል ‹‹ኑ አብረን እንሥራ!›› ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም ባቀረቡት ዩኒቨርሲቲ አቀፍ የምርምር ጉድኝት ገለፃ ዩኒቨርሲቲው በምርምር፣ በማኅበረሰብ ጉድኝት፣ በመማር ማስተማር እንዲሁም በፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር መስኮች ከተለያዩ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ በመጥቀስ በቀጣይም በውሃ ሀብት፣ በግብርና፣ በጤና፣ በቱሪዝምና እንግዳ አቀባበል፣ በማዕድንና ኢነርጂ፣ በአስተዳደራዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም ሌሎቸ ተያያዥ መስኮች ላይ በጋራ ለመሥራት ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውንና ዩኒቨርሲቲውም ጽኑ የትብብር ፍላጎትና እምቅ አቅም እንዳለው ለተሳታፊዎቹ አስረድተዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት ዲን አቶ እንየው ደረሰ በበኩላቸው ት/ቤቱ በተለያዩ መስኮች በትብብር እየሠራ ከሚገኝባቸውና በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ከሚገኙ የፍትህ ተቋማት መካከል ኖርዌይ ኤምባሲ፣ ጣሊያን ሀገር የሚገኘው ማቸረታታ/Macerata/ ዩኒቨርሲቲ፣ የሕንድ ብሔራዊ የሕግ ት/ቤት፣ ጀርመን የሚገኘው ኦክስፎርድ ብሩክስ/Oxford Brookes/ ዩኒቨርሲቲ እና UNHCR ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡ እንደ ዲኑ ገለጻ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም በምርምር፣ በማኅበረሰብ ጉድኝትና መማር ማስተማር ላይ ከት/ቤታቸው ጋር በትብብር እየሠሩ ናቸው፡፡ በቅርቡም ከ UNHCR ጋር በተደረገ ስምምነት በኮንሶ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች፣ በደራሼና በአሌ ልዩ ወረዳዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች፣ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳቶኞች፣ በግጭት ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ነፃ የሕግ አገልግሎት ለመስጠት የትብብር ፕሮጀክት ሥራ መጀመሩንም ዲኑ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ት/ቤቱ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ጋር በመተባበር በዩኒቨርሲቲና በ2ኛ ደረጃና መሰናዶ በት/ቤቶች የሰብዓዊ መብቶች ክበባትን ለማቋቋም፣ ሃንስ ሰይደል ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የሰብዓዊ መብቶች፣ ፍትሕና አስተዳደር ምርምር ማዕከል ለማቋቋም እንዲሁም ከኦክስፎርድ ብሩክስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና በኢትዮጵያ ብቸኛ የሆነ “Forced Migration and Refugees Law” የተሰኘ አዲስ የ2ኛ ዲግሪ የትምህርት

ፕሮግራም ለመክፈት እየተዘጋጀ መሆኑን ዲኑ ጠቁመዋል፡፡ የዕለቱ መርሃ-ግብርም በፕሮግራሙ ከተሳተፉ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት የሚያስችል ግብዓት የተሰበሰበበት ነውም ብለዋል፡፡

በውይቱ ወቅት አስተያየቶቻቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከምርምር ኮንፈራንሱ ባሻገር በትብብር የመሥራት አማራጮች ዙሪያ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረው ሰብዓዊ መብቶችን በማስተዋወቅ፣ የሰብዓዊ መብቶች ቁጥጥር፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃና መከበር፣ በነጻ የሕግ አገልግሎት፣ በምግብ ዋስትና እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት