ስለድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የውሃ ሀብት ግንዛቤ ለመፍጠር በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም ሰኔ 2/2014 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በይፋ ተመሥርቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከሚረዱን ሀብቶች ዋነኛው ስለሆነው የውሃ ሀብታችንና ስለድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚናገሩ ዜጎችና የምንናገርበት መንገድ የተበታተነና ያልተቀናጀ ነው፡፡ አንድም ሌላ ሀገር አቋርጦ ወደ ሀገራችን የሚገባ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ባይኖርም አብዛኞቹ የሀገራችን ወንዞች ድንበር ተሻግረው ወደ ሌሎች ሀገራት የሚፈሱ በመሆናቸው በወንዞቹ ላይ የልማት ሥራዎች ማከናወን ለመንግሥት አስቸጋሪ መሆኑን ዶ/ር ሀብታሙ ጠቁመዋል፡፡ ከታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትና ከደጋፊዎቻቸው ምዕራባውያን ሀገራት የሚቀርቡ ሐሰተኛ ትርክቶችንና በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሠረቱ አሉባልታዎችን በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ የማክሸፍ ሥራ እንዲሠራ የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሚዩኒኬሽን መማክርት ፎረም መመሥረት ማስፈልጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በውሃና ውሃ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ምሁራንና መገናኛ ብዙኋንን በማቀናጀት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ብቻ ሳይሆን የውሃ ሀብትንና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ትኩረት ያደረጉ በተለይ በውጪ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች በቋሚነት በሚዲያዎቻችን ሊቀርቡ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ያሳሰቡት ሚኒስትሩ የተመሠረተው ፎረምም ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ስለውሃ ሀብቶቻችንና ሃይድሮሎጂ መረጃ፣ ስለድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ስለተለያዩ የውሃ መሠረተ ልማቶች ወይም ፕሮጀክቶች ዙሪያ ለሚኒስቴሩ የኮሚዩኒኬሽንና የውሃ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጥ ነው፡፡ የሀገራችን ሕጻናት ስለውሃ ሀብታችንና ስለድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችን ከልጅነታቸው ጀምሮ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጎ ሊሠራ ይገባል ያሉት ዶ/ር ሀብታሙ ይህም በቀጣይ ከታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትና ከምዕራባውያን ሊመጣ የሚችለውን ተፅዕኖ ተቋቁሞ ሀገሩን በዕውቀት የሚጠብቅ ትውልድ ለማፍራት ያግዛል ብለዋል፡፡ የፎረሙ ምሥረታ በሀገራችን በውሃው ዘርፍ በርካታ መሪዎችን፣ ምሁራንንና ባለሙያዎችን በማፍራት ጉልህ ሀገራዊ ሚና እየተወጣ በሚገኘው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መካሄዱ በራሱ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠውና ለዩኒቨርሲቲውም የዘርፉን የመሪነት ሚና በትጋት እንዲወጣ እምነት የተጣለበት መሆኑን እንደሚያመላክት ዶ/ር ሀብታሙ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መሠረቱ የውሃ ምኅንድስና መሆኑን አስታውሰው በሀገራችን የውሃ ሀብት አጠቃቀም ረገድ ትልቅ ፋይዳ ያለው የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም ከብዙ ምክክሮችና ሂደቶች በኋላ በዩኒቨርሲቲያችን በይፋ መመሥረቱ ጉዳዩን ታሪካዊ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ምሥረታውን ለማስተናገድ ያገኘው ዕድልና ቀጥሎም በፎረሙ የሚኖረው ሚና ከውሃ መስክ የልኅቀት ማዕከልነቱ አንጻር መልካም ዕድል ስለሚፈጥር በሚመሠረተው ፎረም ዩኒቨርሲቲው የመሪነት ሚና ወስዶ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ጨምሮ በኢንስቲትዩቱና በዩኒቨርሲቲው ሌሎች ዘርፎች የሚገኙ ምሁራን በፎረሙ በንቃት በመሳተፍ ለፎረሙ የሚደረገውን ድጋፍ እንደ ሀገር አቀፍ ማኅበረሰብ አገልግሎት በመውሰድ በዓመታዊ ዕቅድ ተይዞ ሊሠራ እንደሚገባ ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡

የጋሞ ዘን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው የጋሞ ዞን በጥቅሉ በውሃ ሀብት የበለፀገ አካባቢ ሲሆን በተለይ የዞኑ መዲና የሆነችው አርባ ምንጭ በዓባያና ጫሞ ሐይቆች የተከበበች፣ የኩልፎ ወንዝ በመሃል አቋርጦ የሚያልፍባት፣ ከአርባ በላይ ምንጮች የሚፈልቁባት እንዲሁም በውሃው ዘርፍ ለሀገራችን አለኝታ የሆነውና በርካታ ምሁራንን በማፍራት ቀዳሚ የሆነው የቀድሞው የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአሁኑ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መገኛ መሆኗን ተናግረዋል፡፡ በሀገራችን በሚገኙ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የውሃ ሀብታችን ዙሪያ በምሁራንና በሚዲያዎች መካከል ቅንጅት በመፍጠር በመስኩ ያለውን የኮሚዩኒኬሽን ሥራ በተደራጀ መንገድ ለማከናወን በማሰብ በአርባ ምንጭ ከተማ ብሎም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፎረሙ መመሥረቱ ከተማውም ሆነ ተቋሙ

ከውሃ ጋር ካላቸው ቁርኝት አንጻር ሲታይ ትክክለኛ ምርጫ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ፎረሙ ከምሥረታ ባለፈ ወደ ተግባር ገብቶ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች እንዲሠራና በፎረሙ የሚሳተፉ አካላትም የበኩላቸውን ሚና በትጋት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል አብዛኞቹ የሀገራችን ወንዞች ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው ወንዞቹን መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም ለማዋል በሚሞክርበት ጊዜ ከታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትና ከምዕራባውያን ከፍተኛ የሆኑ ፈተናዎች ሲገጥሙን ቆይተዋል ብለዋል፡፡ ፈተናዎቹን ከመጋፈጥና መፍትሄ ከማበጀት አንጻር በተቋምም ሆነ በግለሰብ ደረጃ በተበታተነ መንገድ ሥራዎች እንደሚሠሩ የተናገሩት ዶ/ር አብደላ ዩኒቨርሲቲያችንን ማዕከል አድርጎ የተመሠረተው ሀገራዊው የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም የተበተታኑ ሥራዎቻችንን አንድ ላይ በማምጣትና በማቀናጀት ድምፃችንን ለዓለም ከፍ አድርገን እንድናሰማ ፋይዳው ጉልህ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አብደላ በተጨማሪም የውሃ ሀብታችንን ለሀገራችን ዕድገትና ብልጽግና ለመጠቀምና የውጭ ጫናዎችን ለመቋቋም የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ከማመላከት እንዲሁም የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትን የበሬ ወለደ ትርክት በምርምር ላይ በተመሠረቱ ትክክለኛ መረጃዎች በማክሸፍ ለዓለም እውነታውን ከማስገንዘብ አንጻር ፎረሙ ያለው ጠቀሜታ በእጅጉ የጎላ ነው፡፡

ፎረሙ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሰብሳቢነት ከስሩ የሚቋቋሙ ንዑስ ክፍሎችን ይዞ በውሃ፣ በውሃ ዲፕሎማሲና ኮሚዩኒኬሽን ላይ ትኩረት አድርጎ ዓመታዊ የምርምር ኮንፈረንሶችን፣ የሩብ ዓመት ዎርክሾፖችንና የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት በዘርፉ ላይ በዘላቂነት የሚሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በፎረሙ ምሥረታ ላይ ከውሃና ኢነርጂ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤቶች፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራንና ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ጉዳይ የአረብኛ ቋንቋ ተሟጋች መሐመድ አል-አሩሲ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮችና ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ ዲኖች፣ ተመራማሪዎች፣ መምህራንና ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት