አርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 20ኛው ‹‹የውሃ ሀብቶች ለዘላቂ ልማት›› ዓለም አቀፍ የምርምር ሲምፖዚየም ላይ እንዲታደሙ ከተጋበዙ ከተለያዩ ተቋማት የመጡ አካላት ጋር ሰኔ 1/2014 ዓ/ም በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ውይይት አካሂዷል፡፡

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል ኢንስቲትዩቱ በ1979 ዓ/ም ተማሪዎችን ተቀብሎ ማሠልጠን መጀመሩን አስታውሰው በወቅቱ ሃይድሮሊክ፣ ኢሪጌሽንና ሳኒታሪ ምኅንድስና በዲግሪና በአድቫንስድ ዲፕሎማ ደረጃ ይሰጡ ነበር ብለዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያ ዲግሪ 4፣ በ2ኛ ዲግሪ 11 እና በ3ኛ ዲግሪ 7 ፕሮግራሞች ያሉት መሆኑን ዶ/ር አብደላ ገልጸዋል፡፡ በውሃ ሀብት ምርምር ዘመኑን የሚመጥኑ ለምርምር ሥራ አጋዥ መሳሪያዎችን አስመጥተን እየገጠምን ነው ያሉት ዶ/ር አብደላ በትብብር ዘርፍ ከስኳር ኮርፖሬሽን፣ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ከሌሎች ተቋማት ጋር እየሠራን ነው ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም አርባ ምንጭ ከተማ፣ ጋሞ ዞንና ዩኒቨርሲቲው ለትብብር ሥራዎች ያላቸው አሁናዊ ምቹ ሁኔታዎች ዙሪያ ባቀረቡት ገለጻ ዩኒቨርሲቲው በተፈጥሮ ሀብቷ በታደለች ከተማ የሚገኝ ሲሆን አብዛኞቹ ካምፓሶችም በአካባቢው የቱሪስት መስህብ በሆኑ ቦታዎች ስም መሰየማቸውን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በ76 የቅድመ ምረቃ፣ በ114 የ2ኛ ዲግሪና በ26 የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግርና በማኅበረሰብ ጉድኝት በጋራ ለመሥራት አካባቢው ምቹና ዩኒቨርሲቲውም ለትብብር በሩ ክፍት ነው ብለዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በአግባቡ እንድትጠቀም የተማረ የሰው ኃይል ማፍራትና ምርምርን ማካሄድ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው በዚህ ረገድ አርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መሠረት የጣለና ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኝ ነው ብለዋል፡፡ በመስኩ ለአንድ ዓላማ ተሰልፎ በትብብር መሥራት በአጭር ጊዜ ከስኬት ለመድረስ እንደሚረዳም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ልዩ አማካሪ አቶ አስቻለው ተስፋዬ በበኩላቸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ በተለይ በውሃ ሳይንስ ልቆ መውጣትና የተሻለ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባልና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አማካሪ አቶ መሐመድ አል-አሩሲ በውይይቱ ላይ በሰጡት አስተያየት በውሃ ዘርፍ ከሚያጋጥሙን ችግሮች አንዱ የውጪ ሚዲያ ተፅዕኖ ነው ብለዋል፡፡ ሚዲያዎቹ በኢትዮጵያ የሚሰጡ ግልጽና ተአማኒ መግለጫዎችን በማዛባትና በማቀያየር በሕዝብና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድሩ መሆኑን አቶ መሐመድ ገልጸዋል፡፡ የሀገራችን ሚዲያዎች መበታተንና ግልጽ አቋም አለመያዝ ችግሩን ማባባሱን የተናገሩት አቶ መሐመድ ሀገራችን ለገጠማት የሚዲያ ጦርነት ሁላችንም ሠራዊት ሆነን መታገል አለብን ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በውሃና ሌሎች ዘርፎች ልቆ በመውጣት የልኅቀት ማዕከል ለመሆን በተለይም ለውሃ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ልዩ አማካሪ አቶ አስቻለው ተስፋዬ፣ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባልና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አማካሪ አቶ መሐመድ አል-አሩሲ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ፣ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማልን ጨምሮ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የአልሙናይ ሰብሳቢና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት