በአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት 20ኛው ዓለም አቀፍ ‹‹ዘላቂ የውሃ ሀብት ልማት›› የምርምር ሲምፖዚየም ከሰኔ 3-4/2014 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡

በዕለቱ ቁልፍ ንግግር ያቀረቡት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ተቋማቸው ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን፣ ከፍተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን፣ የታዳሽ ኃይል ልማት ሥራዎችንና የውሃ ሀብቶችን የማስተዳደር ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ጠቁመው ከዚህም ባሻገር ተቋሙ በ2022 ዓ/ም የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር በመዘርጋት የመጠጥ ውሃና ኢነርጂ አቅርቦት ለሁሉም ዜጋ ተረጋግጦባት በብልጽግና ጎዳና የምትጓዝ ኢትዮጵያን የማየት ራዕይ ሰንቆ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውሃ ሀብትን በዘላቂነት ለማልማት ተቋማቸው ከመዋቅር ለውጥ ጀምሮ በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን በትምህርት፣ በሥልጠናና አቅም ግንባታ፣ በምርምርና በማማከር አገልግሎት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ሀብታሙ የመጀመሪያና የ2ኛ ዲግሪያቸውን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንደተከታተሉና በዩኒቨርሲቲው በመምህርነት እንዳገለገሉ አስታውሰው የዚህ አንጋፋ ተቋም ምሩቅ በመሆናቸው ሁሌም እንደሚኮሩና ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተለየ ቁርኝት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ውሃ ለሰው ልጆችና በምድር ላይ ለሚኖሩ ሕይወት ያላቸው ፍጡሮች ሁሉ በሕይወት ለመቀጠል ወሳኝና መሠረታዊ ሀብት መሆኑን ተናግረው ውሃ ለመጠጥ፣ ለግብርና ሥራና ለኢንደስትሪ መስፋፋት ጠቃሚ የሆነ ሀብት በመሆኑ በተገቢው መንገድ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ከሀገራችን የሕዝብ ቁጥር እድገት፣ ከከተሜነትና ከኢንደስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የምግብ፣ የንጹሕ ውሃና የኃይል አቅርቦትን መጨመር ይገባል ያሉት ዶ/ር ዳምጠው ከዚህ አንፃር የመስኖ ግብርናን ማስፋፋት፣ የንጹሕ ውሃ አቅርቦትን ማሳደግና እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተስማሙ የውሃ ኃይል ግድቦችን በመገንባት የውሃ ሀብታችንን በዘላቂነት ለማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ውሃን ጨምሮ ያሉንን የተፈጥሮ ሀብቶች በዘላቂነት የመጠቀም ጉዳይ የወቅቱ የዓለማችን ትኩረት መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በዘላቂ የውሃ ሀብት ልማትና አስተዳደር ረገድ በሰው ኃይል ልማት፣ አዳዲስ ዕውቀቶችን በማፍለቅና ቴክኖሎጂን በማሻገር የበኩሉን ይወጣል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል ሲምፖዚየሙ ከኢንስቲትዩቱ ምሥረታ ጥቂት ዓመታት ጀምሮ ለ16 ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም ላለፉት 3 ተከታታይ ጊዜያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በሲምፖዚየሙ በውሃ ዘርፍ የተከናወኑ የተለያዩ ምርምር ሥራዎች በፌዴራል፣ በክልልና በዞን ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ውሳኔ ሰጪ አካላትና ምሁራን በሚገኙበት የቀረቡ ሲሆን ይህም የዘርፉን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ውሃን በአግባቡ በዘላቂነት ማልማት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክሮች ተደርገው የመፍትሔ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከምሥረታው ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተሠሩና እየተሠሩ በሚገኙ ታላላቅ የውሃ ፕሮጀክቶች ላይ በአመራርነትና በምኅንድስና ሙያዎች የሚሠሩ በርካታ ምሁራንን ያፈራ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አብደላ በአሁኑ ወቅት ኢንስቲትዩቱ ከመጀመሪያ እስከ 3ኛ ዲግሪ ባሉ ፕሮግራሞቹ በተለያዩ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ መሥራት የሚችሉ በርካታ ምሁራንን በጥራት እያፈራ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ተቋሙ በውሃ ምኅንድስና ዘርፎች፣ በማኅበረሰብ ተኮር ምርምር እንዲሁም የተለያዩ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶችን በማማከር ሥራ ላይ የልህቀት ማዕከል ለመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሠራ መሆኑንም ዶ/ር አብደላ ጠቁመዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ ከቀረቡ ጥናቶች መከከል ‹‹Hydropower in Ethiopia and Opportunities and Challenges›› በሚል ርዕስ በዶ/ር ሙሉጌታ በረደድ የቀረበው አንዱ ሲሆን በጥናቱ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ከዲሞክራቲክ ኮንጎ በመቀጠል ሁለተኛዋ ግዙፍ የውሃ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላት ሀገር መሆኗን ጠቁመዋል፡፡ ካለው የውሃ ኃይል የማመንጨት አቅም 90 ከመቶው እስከ አሁን አልተነካም ያሉት ተመራማሪው መልክዓ ምድሩና በደጋማው አካባቢ ያለው ዝናባማ የአየር ሁኔታ አነስተኛ፣ መካከለኛና ግዙፍ የኃይል ማመንጫዎችን በቀላል ወጪ መገንባት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ዕምቅ ሀብት እንዳንጠቀም እንደ ሀገር ያለብን የገንዘብ እጥረት እንዲሁም የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ለሥራው ተባባሪ አለመሆናቸው ዋነኛ ማነቆዎች መሆናቸውን አጥኚው አመላክተዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ምሁራንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን በ6 ጭብጦች ላይ ያተኮሩ 24 የምርምር ሥራዎች በመድረክ፣ በፖስተርና በኦንላይን ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸውል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት