የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት ት/ክፍል ከጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር በወጣቶች ሰብእና ግንባታ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በአመራር ክሂሎት ዙሪያ በጨንቻ ወረዳ ለሚገኙ ወጣት አደረጃጀቶች፣ ኢንተርፕራይዞችና ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ሰኔ 3/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም አይካ እንደገለጹት ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለልማት፣ ለሰላምና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የወጣቱ ድርሻ የላቀ በመሆኑ ሥልጠናው በወጣቱ መካከል የአመለካከት፣ የግንዛቤ፣ የዕውቀትና የሀብት አጠቃቀምን ለማሳደግ ያለመ ነው፡፡ ወጣቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው በአስተሳሰብ፣ በአመራርና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያላቸውን አመለካከት የሚያሳድጉበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ወ/ሮ አስቴር ሰይፉ ዩኒቨርሲቲው በሥልጠናና በተለያዩ ሥራዎች ማኅበረሰቡን እያገለገለ መሆኑን ጠቅሰው ለሀገር እድገት ወጣቱ ጉልህ ድርሻ ያለው በመሆኑ የዕውቀት አድማሱን ለማስፋት የተዘጋጀ ሥልጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የማኔጅመንት ት/ክፍል መምህርና አሠልጣኝ መሐመድ አረብ የአመራር ምንነት፣ የሚጠበቅበት ሥራና ሌሎችን የሚያነሳሳበት መንገድ እንዲሁም ራስን፣ ቡድንንና ድርጅትን መምራት ላይ ሥልጠና መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የት/ክፍሉ መምህርና አሠልጣኝ ተዛና በቀለ በበኩላቸው ሥልጠናው በዋናነት ውስጣዊ ተነሳሽነት ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረው ኢንተርፕራይዞች ያላቸው አመለካከትና የሥራ ተነሳሽነት እንዲሁም ለቢዝነስ ስኬትና ውድቀት የሚያበቁ ባህሪያትና ሌሎችም በሥልጠናው ተዳስሰዋል ብለዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል ወጣት ጌታሁን ሲሳይ ሥልጠናው ከዚህ በፊት በልምድ የሚሠራውን ሥራ በዕውቀት እንዲመራ የሚያደርግ መሆኑን ተናግሯል፡፡ የወጣቶች ፌዴሬሽን ም/ፕሬዝደንት ወጣት ታረቀኝ ግርማ በበኩሉ ከሥልጠናው የአመለካከት ለውጥና አብሮ የመሥራት ግንዛቤ ማግኘቱን ተናግሯል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት