የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና የእንግሊዝ ተራድኦ ድርጅት (FCDO) ድጋፍ የሚያደርጉለት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጁት የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስር የምርምር ውጤቶች ወደ ገበያ የሚገቡበት የገንዘብ ድጋፍ ውድድር ላይ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አሸናፊ ሆኗል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በውድድሩ ላይ ከ20 ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ 49 ውጤታማ፣ የተጠናቀቁ እና ወደ ገበያ ሊገቡ የሚችሉ የምርምር ውጤቶች የቀረቡ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው የባዮቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ‹‹Popularization and Commercialization of Innovative Enset Technologies and Two Products›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ንደፈ ሃሳብ ከተወዳዳሪዎች መካከል አንደኛ ደረጃን በማግኘት አሸናፊ ሆነዋል፡፡

ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ውድድሩ ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት መሆኑን አስታውሰው ውድድሩን ከማሸነፍ ባሻገር ከዳኞች የተሰጠው ግብረ መልስ በእጅጉ አበረታችና ለቀጣይ ሥራ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል፡፡ የምርምር ውጤቶችን ወደ ገበያ ለማስገባት የሚያስችለውን የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ያስችል ዘንድም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ዶ/ር አዲሱ ገልጸዋል፡፡

ለሥራው ሙከራ ጊዜ የሚሆን የግማሽ ሚሊየን ብር ድጋፍ መገኘቱን የጠቆሙት ዶ/ር አዲሱ በገንዘብ ድጋፉ አርሶ አደሮችን በማሠልጠን በዘመናዊ መንገድ የተመረቱ የእንሰት ውጤቶችን በናሙና ደረጃ ወደ ገበያ የማስገባት ሥራ የሚሠራ ሲሆን በሙከራ ጊዜው ውስጥ ውጤታማ መሆን ከተቻለ ተጨማሪ ከ10 እስከ 15 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት