አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በ2ኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች በመደበኛ፣ በማታ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት፣ እንዲሁም በ3ኛ ዲግሪ በመደበኛ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2,561 ተማሪዎችን ሰኔ 25/2014 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 662ቱ ሴቶች ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የኢትዮጵያን እድገትና ክብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሀገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበረሰብና ምሩቃን ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሀገር ሰላምን ለማደፍረስ የሚሰራጩ እኩይ ተልዕኮዎችን ሳያስተናግዱ በስኬት አጠናቀው ለምረቃ በመብቃታቸው አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ይህን መልካም ሥነ ምግባር በማስቀጠል በሚሄዱበት የሀገራችን አካባቢዎች ሁሉ ለሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ቅድሚያ ሰጥተው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አደራ ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ6 ካምፓሶች በ75 የመጀመሪያ፣ በ114 የ2ኛ እና በ26 የ3ኛ ዲግሪ በአጠቃላይ ከ25 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሃ ግብሮች በማስተማር ላይ ሲሆን የዛሬዎቹን ተመራቂዎች ጨምሮ ዩኒቨርሲቲው ከ72 ሺህ በላይ ምሩቃንን ማፍራቱን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባልና የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ፈጠነ ተሾመ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልእክት ትምህርት ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ቁልፍ መሣሪያ እንዲሁም የማይከስር ሀብት መሆኑን በመገንዘብ እንዲሁም የሀገራችንን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመረዳት ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው በንድፈ ሃሳብና በተግባር ያገኙትን ዕውቀት በሚሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ ለዘላቂ እድገትና ሽግግር እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን /አልሙናይ/ ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ ኤርሚያስ ዓለሙ ተመራቂዎች በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት በተግባር ውጤታማ ለማድረግ ብዙ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ተናግረው በቀጣይ ራሳቸውን ለማሻሻል እንዲሁም ያስተማራቸውን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና ሀገር ለማገልገል በታማኝነትና በትጋት እንዲሠሩ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን አባል በመሆን ለአካባቢው ማኅበረሰብና ለዓለም መልካም አስተዋጽኦዎችን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራልና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባል፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እጩ ምሩቃንን ለምረቃ በማቅረብ አስመርቀዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት